ትውልዱ አረጋውያንን ማክበር፣ ማድመጥ እና ችግር ላይ የወደቁትን ደግሞ መደገፍ እንደሚገባ ተጠየቀ።

44

ባሕር ዳር: ጥቅምት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ መስከረም 21 ቀን ይከበራል፤ የአረጋውያን ቀን። በዓለም ለ33ኛ ጊዜ እና በኢትዮጵያ ለ32ኛ ጊዜ “የአረጋውያንን መብት ማክበር ትውልድ ለማሻገር” በሚል መሪ ሃሳብ ተከብሯል። በአማራ ክልልም በተለያዩ ችግሮች ሳይከበር የዘገየው የዘንድሮው የአረጋውያን ቀን ዛሬ ተከብሯል።

አረጋውያንን በዘላቂነት ከመደገፍ ባለፈ
በእድሜ ዘመናቸው ያካበቱትን እውቀት እና ልምድ ለሀገር ግንባታ እንዲያውሉ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባም ተጠይቋል።

የአረጋውያን ቀን ሲከበር ለሀገር ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በመዘከር፣ ያሉባቸውን ችግሮች ደግሞ መፍታት ላይ ያተኮረ ሊኾን እንደሚገባ የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ንጹህ ሽፈራው ገልጸዋል።

ምክትል ኀላፊዋ እንዳሉት አሁን ላይ በርካታ አረጋውያን ጧሪና ደጋፊ በማጣት ለተለያዩ ማኅበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ችግሮች ተጋልጠዋል፤ ለመብት ጥሰትና ለሥነ ልቦና ቀውስ ተዳርገዋል።

ቢሮው የአረጋውያንን ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና መብታቸውን ለማስከበር ባለፉት ዓመታት የተለያዩ ሥራዎችን ሲሰራ ቆይቷል። ከዚህም ውስጥ በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በሚገኘው የአረጋውያን የገቢ ማስገኛ ማዕከል ከሚገኝ ገቢ ለ1550 ጧሪና ደጋፊ ለሌላቸው አረጋውያን በየወሩ የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገ ነው።

የገቢ ማስገኛ ማዕከሉን ከባሕር ዳር ባለፈ በሌሎች አካባቢዎችም ለማስፉት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

ከ155 ሺህ በላይ አረጋውያን ደግሞ በገጠር እና ከተማ ልማት ሴፍትኔት መርሐ ግብር ተጠቃሚ ኾነዋል። በጎ ፈቃድን በማስፋት ለአረጋውያን ቋሚና ጊዜያ ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝም ነው ምክትል ኀላፊዋ የገለጹት።

እንዲሁም በርካታ ተጋላጭ አረጋውያንን የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድን መርሐ ግብር ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል።

የአረጋውያን ድጋፍ እና እንክብካቤ ለአንድ አካል ብቻ የሚተው ሳይኾን ከቤተሰብ ጀምሮ መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት ጭምር ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ ጠይቀዋል። መንግሥታዊ ተቋማትም የአረጋውያንን ጉዳይ በእቅዳቸው በማካተት ማኅበራዊ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

አረጋውያን በእድሜ ዘመናቸው ያካበቱትን እውቀትና ልምድ በመጠቀም የተፈጠሩ ችግሮች እንዲፈቱ፣ ትውልድን እንዲያንጹ እና ባሕላዊ እሴቶችን ማስረጽ እንድችሉ ልዩ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ጠይቀዋል።

በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አሥተባባሪ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) የአሁኑ ትውልድ ብድር ከፋይ ሊኾን ይገባል ብለዋል።

ለሀገር ነጻነት ዋጋ የከፈሉ አረጋውያንን ማክበር፣ ማድመጥ፣ ችግር ውስጥ የወደቁትን ደግሞ መደገፍ ከዚህ ትውልድ ይጠበቃል ነው ያሉት። የአሁኑ ትውልድም ስለ ሀገር ፍቅር፣ አርበኝነት አረጋውያንን መጠየቅ እና ተሞክሮውንም መቅሰም ይገባል ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአምራች ዘርፉ የሥራ እድል በመፍጠር የሀገር ውስጥና የውጭ ተወዳዳሪነትን ለማጎልበት በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ።
Next article“ቦርከና መቀነቷ፣ ሐረጎ ጉልላቷ”