በአምራች ዘርፉ የሥራ እድል በመፍጠር የሀገር ውስጥና የውጭ ተወዳዳሪነትን ለማጎልበት በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ።

49

አዲስ አበባ፡ ጥቅምት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማሳደግና ለማበረታታት ያለመ ውይይት ከግል ባለሃብቶች ጋር እያካሄደ ነው።

በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ያሉ የግብዓትና የመሰረተ ልማት ማነቆዎችን በተመለከተ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተቀነባበሩ የምግብ ምርቶች ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሽመልስ አድማሱ ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከፍተኛ ወጪ ተደርጎባቸው ከውጭ ከምታስገባቸው ምርቶች መካከል የተቀነባበሩ ምግቦች ትልቁን ቦታ ይይዛሉ ብለዋል።

ይሄንን ለማስቀረት እና የሀገር ውስጥ አምራች ዘርፉን ለማበረታታት እንዲሁም የሀገሪቱን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እራሱን የቻለ ምግብን ከማምረት ጀምሮ አቀነባብሮ ለገበያ ማቅረብ የሚችል ተቋም በሚኒስቴር ደረጃ መቋቋም አለበት የሚል ምክረ ሃሳብን አቅርበዋል።

ፕሮፌሰሩ የአምራቹን ዘርፍ በውጤታማነት ለመጠቀም የኢትዮጵያን ታምርት ንቅናቄ ከአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ትስስር ጋር ማቀናጀት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሀሰን መሐመድ ኢትዮጵያን ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ለምታደርገው የኢኮኖሚ ሽግግር በአምራች ዘርፉ የሚስተዋሉ የግብዓት እና የመሠረተ ልማት ችግሮች ለመቅረፍ በቅንጅት መሥራት ይገባል ብለዋል።

በውይይቱ የሚቀርቡ ሃሳቦች በግብዓትነት ተካተው በዘርፉ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት እንደሚሠራም ተገልጿል።

ዘጋቢ፦ ቤተልሄም ሰለሞን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ኾኖ ሲደራጅ ኅብረ ብሔራዊቷን ኢትዮጵያ ለመመሥረት እና በጋራ ለመቆም የሚያግዝ ጅማሮ ይኾናል በሚል እምነት ነው” የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next articleትውልዱ አረጋውያንን ማክበር፣ ማድመጥ እና ችግር ላይ የወደቁትን ደግሞ መደገፍ እንደሚገባ ተጠየቀ።