
ባሕርዳር፡ ጥቅምት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “አዲስ ምዕራፍ እና አዲስ ተስፋ ለአዲስ ክልል” በሚል መሪ ሃሳብ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ምስረታ ሥነ-ሥርዓት እየተከበረ ነው፡፡ በምስረታ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ሕዝብ ለአኹናዊቷ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ አስተማሪ ሕዝብ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ኀብረ ብሔራዊ አንድነቷ እና አብሮነቷ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሕዝብን ጥያቄ መመለስ ያስፈልጋል ያሉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ዘመኑን በዋጀ እና በሰለጠነ መንገድ ስላቀረባችሁ ከልብ ትመሰገናላችሁ ብለዋል፡፡
ማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ኾኖ ሲደራጅ ኅብረ ብሔራዊቷን ኢትዮጵያ ለመመሥረት እና በጋራ ለመቆም የሚያግዝ ጅማሮ ይኾናል በሚል እምነት ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የአማራ ክልል ሕዝብ እና መንግሥት አዲሱን ክልል ለማገዝ ከጎኑ እንደሚቆምም አረጋግጠዋል፡፡
የአማራ ክልል ወቅታዊ ፈተናዎች የበዙበት መኾኑን ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ይገነዘባሉ ያሉት ርእስ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አዲሱን ክልል ለማቋቋም የ30 ሚሊየን ብር ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡
በታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!