
ባሕር ዳር: ጥቅምት 17/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ቢሮው በቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ ከቱሪዝም ዘርፉ የሚጠቀሙ፤ በክልሉ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ዘርፎች ዙሪያ የሚመለከታቸው ሁሉ ለክልሉ ዘላቂ ሰላም በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርቧል።
“ጪስ አልባው ኢንዱስትሪ” የሚል ተጨማሪ ስያሜ የተቸረው ቱሪዝም ለሉላዊቷ ዓለም ልዩ ገፀ-በረከት ነው። በዓለም የቱሪዝም እንቅስቃሴ የመንፈስ ሃሴትን እና የቀደምት እውቀትን ለሚሹ ሁሉ ኢትዮጵያ ልዩ መዳረሻ ነች።
አያሌ መልካ ምድራዊ፣ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ እና መንፈሳዊ የቱሪስት መዳረሻዎችን ያቀፈችው ኢትዮጵያ የዓለም ቱሪዝም ሙዚየም ተደርጋ ትወሰዳለች።
ኢትዮጵያ በርካታ የዓለም ሕዝብ ሃብት እና ንብረት የኾኑ ቅርሶችን በተባበሩት መንግሥታት የትምህር፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማስመዝገብ ከቀዳሚዎቹ የአፍሪካ ሀገራት ተርታ የመጀመሪያዋ ናት።
ከሀገሪቱ የቱሪስት መዳረሻ መስህቦች መገኛ መካከል ደግሞ የአማራ ክልል በርካታ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች ካላቸው አካባቢዎች አንዱ እና ቀዳሚው ነው።
የቱሪዝም ዘርፉ የሀገርን ገቢ ከማሳደግ ባለፈ በቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር የሚችል መስክ ነው። በአማራ ክልል በቱሪዝም ላይ ብቻ የተመሠረተ ሕይዎት ያላቸው ግለሰቦች ብቻ ሳይኾኑ ከተሞች ጪምር ናቸው።
ባለፉት ስድስት ዓመታት በዓለም ዙሪያ፣ በኢትዮጵያ እና በክልሉ የተፈጠሩ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ዘርፉን ክፉኛ ጎድተውታል። ላሊበላ፣ ጎንደር፣ ደባርቅ እና ባሕር ዳርን ጨምሮ ከወትሮው የዓለም ጉራማይሌ ሕዝብ የሚተምባቸው አካባቢዎች ቱሪስትን ከናፈቁ ውለው አድረዋል።
የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ ጣሂር ሙሐመድ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ባለፉት ስድስት ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኾሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተከሰተው ጦርነት ዘርፉ ክፉኛ ተጎድቷል።
ኀላፊው እንዳሉት ከ2000 ዓ.ም እስከ 2008 ዓ.ም በክልሉ የነበረው የጎብኝዎች ፍሰት እና የገቢ መጠን በየዓመቱ ከ10 እሰከ 15 በመቶ እድገት አሳይቶ ነበር። ከ2011 ዓ.ም በኋላ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተከሰተው ጦርነት ምክንያት ዘርፉ ክፉኛ ተጎድቷል።
በ2015 ዓ.ም በክልሉ አንጻራዊ ሰላም ቢኖርም የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ፍሰት ግን ከ30 ሺህ የበለጠ አልነበረም ተብሏል። ከ2016 በጀት ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ ደግሞ በክልሉ የተከሰተው የውስጥ ሰላም መደፍረስ ዘርፉን “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ኾኖበታል።
በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ብቻ ኑሯቸው የተመሠረተ የኅብረተሰብ ክፍሎች ችግር ላይ ወድቀዋል ነው ያሉት ኀላፊው። የቱሪዝም ኢንዱስትሪው አገልግግሎት ሰጪ ተቋማት የሥራ እንቅስቃሴ በመቀዛቀዙ ለሰራተኞቻቸው ደመወዝ ለመክፈል መቸገራቸውን እና መንግሥትም ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ገቢ አጥቷል ብለዋል።
የቱሪዝም ዘርፉ በየጊዜው በሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮች እየፈተነ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ጣሂር ሙሐመድ ዘርፍ ወደ ነበረበት ከፍታ እንዲያንሰራራ እና እንዲነቃቃ በጋራ መሥራትን ይጠይቃል ብለዋል።
ማኅበረሰቡ፣ የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት እና ከዘርፉ በቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ የኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሁሉ ለሰላም እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!