“በመስኖ ልማት ከ40 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል” ግብርና ቢሮ

64

ባሕር ዳር: ጥቅምት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በተያዘው በጀት ዓመት በመስኖ ከ40 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል።

በ2016 በጀት ዓመት በአንደኛው እና በሁለተኛው ዙር መስኖ በድግግሞሽ ከ333 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር እንደሚሸፈን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የአትክልት እና ፍራፍሬ መስኖ ውኃ አጠቃቀም ዳይሬክተር ይበልጣል ወንድምነው ተናግረዋል፡፡

ከዚኽም ከ40 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት መታቀዱን ነው ያስገነዘቡት። በመስኖ ከሚሸፈኑ ሰብሎች መካከልም ሰፊውን ቁጥር የሚይዘው ስንዴ መኾኑንም ጠቁመዋል።

በነባር ከ280 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት፣ በአዲስ ደግሞ 53 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መለየቱንም ተናግረዋል። እስካሁን 27 ሺህ ሄክታር መሬት የታረሰ ሲኾን ከዚህ ውስጥ 14 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ጠቁመዋል።

በዚኽ ዓመት እስከ ሦስተኛ ዙር በመስኖ ለማልማት መታቀዱንም አስረድተዋል። ሥራው 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋልም ተብሏል።

የግብዓት አቅርቦት ችግር እንዳይፈጠር ሰላም ባለባቸው አካባቢ ከቦታ ቦታ የማጓጓዝ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን ጠቁመዋል።

የካናል ጥገና፣ የጠረጋ ሥራ፣ የውኃ ምንጮችን የመለየት ሥራ እየተሠራ መኾኑንም አቶ ይበልጣል ተናግረዋል።

ዘጋቢ: – ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሀዲያ ነፈራ ደምቋል።
Next articleየኢትዮጵያዊው ጀግና ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ ሐውልት የሀድያ ሌላው ድምቀት