
ደብረ ብርሃን: ጥቅምት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የተቀናጀ የመከላከል ሥራ በማከናወን ግሪሳ ወፍ በሰብል ላይ ሊያደርስ የነበረውን ከፍተኛ ጉዳት መቀነስ መቻሉን የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ ገለጸ፡፡
በዞኑ በ2015/16 የመኸር ምርት ከ496 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በተለያዩ ሰብሎች መሸፈን መቻሉን የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ አስታውቋል፡፡
በአሁኑ ወቅት 122 ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍን ሰብል ለስብሰባ ዝግጁ መኾኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ ኀላፊ ታደሰ ማሙሻ ተናግረዋል፡፡
ኀላፊው አሁን እየጣለ ያለው ዝናብ በደረሰው ሰብል ላይ የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ማኅበረሰቡ ባለው ጠንካራ ማኅበራዊ መስተጋብር ታግዞ በጋራ መሰብሰብ እንዳለበት ነው ያሳሰቡት፡፡
አመቺ በኾኑ አካባቢዎች ባለሃብቶች ዘመናዊ የሰብል መሰብሰቢያና መውቂያ ማሽን በማቅረብ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም አቶ ታደሰ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሰብል ላይ የሚያስከትለው ብክነት ከፍተኛ መኾኑን የገለጹት አቶ ታደሰ ትርጉም ያለው ድጋፍ በማበርከት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
አቶ ታደሰ በዞኑ በ8 ወረዳዎች ውስጥ በ61 ቀበሌዎች ላይ በተቀናጀ የመከላከል ሥራ በማከናወን የተከሰተው ግሪሳ ወፍ ሊያደርስ የነበረውን ከፍተኛ ጉዳት መቀነስ መቻሉን ገልጸዋል። ባሕላዊ የመከላከያ አማራጮችን እና በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት በማካሄድ ግሪሳ ወፉ ሊያስከትል የነበረውን ጉዳት ቀንሰናል ነው ያሉት።
ዞኑ ክልል ግብርና ቢሮ እና ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር አሁንም የመከላከል ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ኀላፊው ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ስንታየሁ ኃይሉ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!