
ባሕርዳር፡ ጥቅምት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 25ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ አመለከተ።
የምክር ቤቱ 25ኛ መደበኛ ስብሰባ ውሳኔዎች፡-
1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው በግል ዳታ ጥበቃ ረቂቅ አዋጅ ነው፡፡ በሀገራችን ግለሰቦች በግል መረጃዎቻቸው ላይ ያላቸውን መብት በዝርዝር የሚደነግግ ሕግ ባለመኖሩ፣ የአገራችንን የግል ዳታ ጥበቃ ሥርዓት ዓለማአቀፋዊ ደረጃዎችን በጠበቀ መልኩ በመገንባት ፋይዳው ዘርፈ ብዙ በመሆኑ እንደዚሁም የግል ዳታ ጥበቃ ባህልና አሠራርን በማጎልበት ተዋናይ በሆኑ አካላት መብትና ግዴታ የሚደነግግ የሕግ ማዕቀፍ እና የማስፈጸሚያ ሥርዓት በመዘርጋት ውጤታማ የሆነ የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት የግል ዳታ ጥበቃ አዋጅ አስፈላጊነት የታመነበት በመሆኑ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
2. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው በገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ ላይ ሲሆን የአርሶ አደሩን፣ ከፊል አርብቶ አደሩን እና የአርብቶ አደሩን የኑሮ ደረጃ አገሪቱ ከደረሰችበት ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ እድገት ጋር ለማጣጣም እንዲቻል የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ሥርዓት መዘርጋት ስለሚገባ፣ የባለመብቶችን የይዞታ ዋስትና ማጠናከር የሚያስፈልግ በመሆኑ፣ የገጠር መሬት ምዝገባና መረጃን ጥራቱን በጠበቀ መልኩ በማደራጀት ከመሬት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የሚነሱ አለመግባባቶች የሚፈቱበትን ስርዓት ማበጀት የሚገባ በመሆኑ፣ የተለያዩ የሀገሪቱን የስነ ምህዳር ቀጠናዎችን ያገናዘበ ዘላቂ የገጠር መሬት አጠቃቀም ስርዓት በመዘርጋት የዛሬው ትውልድ ተጠቃሚነት የመጪውን ትውልድ ጥቅም የማይጎዳ መሆኑን የሚያረጋግጥ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
3. በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው በልዩ ኢኮኖሚ ዞን ረቂቅ አዋጅ ላይ ሲሆን አሁን በስራ ላይ ያለዉን የኢንደስትሪ ፓርኮች ሥርዓት ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ሥርዓት በማሸጋገር የአገራችንን ኢኮኖሚ እድገት ፍጥነት ማላቅ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ የልዩ ኢኮኖሚ ዞን መርሃ ግብር ቀልጣፋ እና አመቺ የኢንቨስትመንት እና የንግድ ከባቢ ሁኔታ ለመፍጠር አይነተኛ መሳሪያ መሆኑ ስለታመነበት፣ የአገራችንን በዓለምአቀፍ የንግድ እሴት ሰንሰለት ተጠቃሚነት ለማጎልበት፣ በቀጠናዊ የንግድ ትስስር ውጤታማ በሆነ መንገድ የመወዳደር አቅማችንን ለማጠናከር እንዲሁም አዋጭ እና ስትራቴጂያዊ በሆኑ አካባቢዎች የሚመሰረቱ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችን ልማት አስተዳደር እና ቁጥጥር የሚመራ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!