
ባሕር ዳር: ጥቅምት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በ12 ሚሊየን ብር ያስገነባቸውን 20 ክፍል ቤቶችን አቅም ለሌላቸው ተጠቃሚዎች አስተላልፏል።
ወይዘሮ አዲሴ ጸጋ በባሕር ዳር ከተማ ለ27 ዓመታት ኖረዋል። አሁን ላይ አራት ልጆችን ለማሳደግ እንጀራ በመጋገር እና የጠላ እህል በማዘጋጀት እንደሚተዳደሩ ተናግረዋል። የከተማ አሥተዳደሩ የቤት ባለቤት ስላደረጋቸው ደስተኛ መኾናቸውን ገልጸዋል።
የስድስት ልጆች አሳዳጊ የኾኑት ወይዘሮ አማረች እንግዳው በኪራይ ቤት ይኖሩ በነበረበት ጊዜ የኪራይ መክፈያ ጊዜ ሲያልፍ ያለው ሰቀቀን ከፍተኛ መኾኑን ነው የገለጹት። አሁን ላይ የቤት ባለቤት መኾናቸው እና ችግራቸው ስለተቀረፈ ደስ እንዳላቸው ተናግረዋል።
ሁለት ልጆች ለማሳደግ ብዙ ውጣ ውረድ አልፌያለሁ፤ ባለቤቴ ስለሞተብኝ ልጅ ለማሳደግ እቸገር ነበር፤ አሁን ላይ የቤት ችግሬ ስለተፈታልኝ ደስ ብሎኛል ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ትዕግስት ምሥጋናው ናቸው።
በባሕር ዳር ከተማ በግሽ ዓባይና ዳግማዊ ክፍለ ከተሞች በሁለት ሳይቶች እያንዳንዳቸው 10 ክፍል ያሏቸው የሁለት ብሎኮች ግንባታ እና የ20 ቤቶች ጥገና መፈጸሙን የከተማው ቤቶች ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ በፍቅሩ በዙ ገልጸዋል።
ለቤቶቹ ግንባታና ጥገና 10 ሚሊዮን ብር ከመንግሥት እና 2 ሚሊዮን ብር ከግል ባለሃብቶች በድምሩ 12 ሚሊዮን ብር ወጪ መኾኑን ነው አቶ በፍቅሩ የተናገሩት። የቤት ባለቤት የኾኑትም አነስተኛ ገቢ ያላቸው ወገኖች መኾናቸውንም ነው የተናገሩት።
በርክክቡ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው መንግሥት ቅድሚያ ለዜጎች መኖሪያ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ገልጸዋል። ከባለሃብቶችና ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር አነስተኛ ገቢ ያላቸው ወገኖችን የቤት ባለቤት እንዲኾኑ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
የኑሮ ውድነትን ሊያቃልሉ የሚችሉ ሌሎች የልማት ሥራዎችም በመንግሥትና በኅብረተሰቡ ትብብር መሠራታቸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ከንቲባው የተናገሩት።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ”ባገኘነው ቤት በሰላም ገብተን መኖር የምንችለው አካባቢያችን ሰላም ሲኾን ነውና አሁን የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ማስቀጠል ያስፈልጋል” ብለዋል።
የጸጥታ ችግር ሲኖር የኑሮ ውድነትም የዚያኑ ያክል እንደሚከፋ ያመላከቱት ከንቲባ ጎሹ ሁሉም ሰው ለሰላም መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል።
ጥያቄዎቻችን በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ መፍታት እንጂ በሁከትና ብጥብጥ የሚፈታ ችግር ስለሌለ ለሰላም ትኩረት እንስጥ ሲሉም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!