
ደሴ: ጥቅምት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አንዳንድ ሰዎች አሉ መከራ የሚያጠነክራቸው፣ ፈተና የሚያበረታቸው፣ ችግር የሚያጸናቸው፣ መገፋት የማይጥላቸው፣ መሰናክል የማያስቆማቸው። ተስፋ እናስቆርጣቸዋለን ሲሉ እልፍ ተስፋ የሚመላባቸው። ብዙ አስቸጋሪ ፈተናዎች ገጥመዋቸዋል፣ ተፈትነዋል፣ በፈተና ግን አልወደቁም። ፈተና አበርትቷቸው፣ ችግር አጠንክሯቸው፣ የተሻለ ለመሥራት ጠነከሩ እንጂ።
ለታላቅ ተቋም ታላቅ ኀላፊነት ተሰጣቸው፣ ታላቅ አደራ ተጣለባቸው። ጊዜው መከራ የበዛበት፣ ፈተና ያየለበት፣ ከችግር ላይ ችግር የሚደራረብበት ነበር። ብርቱ መሪዎች በክፉ ቀን ይገኛሉ፣ በአስሸጋሪ ዘመን በእልህ ይሠራሉ፣ በፈተና ወቅት የበለጠ ይጠነክራሉና እሳቸው በፈተና ወቅት በትጋት ሠሩ፤ በትጋትም አሠሩ።
ለታላቁ ተቋም በተመረጡበት ጊዜ ሀገር ፈተና የበዛባት፣ ጦርነት ያየለባት ወቅት ነበር። መሪዎች ተረጋግተው አይሠሩም። ሕዝብም ተረጋግቶ አይኖርም ነበር። በእርግጥ አሁንም የተሟላ ሰላም የለም። ችግሮች አሁን ድረስ አሉ።
በዚያ ወቅት በርካታ ፈተናዎች ነበሩ። እሳቸው ወደ ኀላፊነት በመጡበት ጊዜ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ተክዶ ጦርነት የተቀሰቀሰበት ነበር። በዚያ ጦርነት ብዙዎች ሞተዋል፣ ብዙዎች ቆስለዋል፣ ደምተዋል፣ ብዙዎች ተሳደዋል። ሃብትና ንብረታቸውን አጥተዋል። መከራና ስቃይም አይተዋል።
ዶክተር ሃይማኖት አየለ ይባላሉ። የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ናቸው። ደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ሐምሌ 12/1954 ዓ.ም የተመሠረተ ታላቅ ተቋም ነው።
በሆስፒታሉ ውስጥ “ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ ለሕዝባቸው ጤና ይህን የአስፋው ወሰን ኃይለ ሥላሴ ሆስፒታልን በሐምሌ 12/1954 ከፈቱ” የሚል ጽሑፍ ተቀርጾ ይገኛል።
ግርማዊነታቸው በልጃቸው ስም ያስገነቡት ሆስፒታል ለበርካታ ዓመታት ለሕዝብ ጤና አገልግሎት ሲሰጥ የኖረ አንጋፋ ተቋም ነው። መንግሥት ሲቀያየር፣ ሥርዓት ሄዶ ሥርዓት ሲመጣ በዛ ሆስፒታል ውስጥ ሐኪምና ታካሚ እየተገናኙ ረዘም ያሉ ዓመታት ነጉደዋል።
ዶክተር ሃይማኖት ለዚህ ታላቅ ተቋም መሪነት የተመረጡ የመጀመሪያዋ ሴት ናቸው። በጤናው ዘርፍ ከ25 ዓመታት በላይ አገልግለዋል። በተጓዙባቸው ረዘም ያሉ ዓመታት በርካታ ውጣ ውረዶችን አሳልፈዋል። ደሴ ሆስፒታል የተማሩበት ቤታቸው ነው። ለቤቱ እንግዳ አይደሉም። ነገር ግን ሆስፒታሉን መምራት አስቸጋሪ እንደኾነም ያውቃሉ።
ወደ ኀላፊነት የመጡበትን ጊዜና ስለ ሆስፒታሉ ሲነግሩኝ “ቤቱን አውቀዋለሁ ግን በጣም ነው የምፈራው፣ ብዙዎቹ መምህራኖቼ ናቸው፣ የምወጣውም አይመስለኝም ነበር። ከባድ ቤት እንደኾነ አውቃለሁ። በሌሎች ተቋማት ሠርቻለሁ። በጣም የምፈራው ደሴ ሆስፒታልን ብቻ ነው። ተጠይቄም አልገባም ያልኩበት ጊዜ ነበር። ሕክምና ተምሬ ስጠየቅ ዝም ብዬ ልሞክረው ብዬ እንጂ እንደዚህ እሠራለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር” ነው ያሉን።
እንደ ደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ያሉ ሆስፒታሎችን መምራት ከባድ እንደኾነም ነግረውናል። ሆስፒታሉ የአፋርና የትግራይ ክልሎችን ጨምሮ የምሥራቅ አማራ ነዋሪዎች አገልግሎት የሚፈልጉበት በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ዜጎች አገልግሎት የሚሰጥ ታላቅ ተቋም ነው።
ሆስፒታሉ ከ10 ሚሊዮን በላይ ለሚኾን ሕዝብ አገልግሎት የሚሰጥ ጫና ያለበት ሆስፒታል እንደኾነም ነግረውናል። የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሚያስተናግደው ሕዝብ ብዛት ከአንዳንድ ሀገራት ሙሉ የሕዝብ ብዛት በላይ ነው።
ሁልጊዜም በርካታ ታካሚዎችን ይቀበላል። ሲያስተናግድ ውሎ ያድራል። ይህ ለሰዓታት ወይም ለቀናት አይደለም ለዓመታት የዘለቀ ነው እንጂ።
“ከበሩ ጀምረህ ተጠንቅቀህ ካልሠራህ፣ ሥራ መሥራት አትችልም። ነገር ግን ሁሉም አጋዥ ነው” ነው ያሉን ዶክተር ሃይማኖት ስለ ሆስፒታሉ ሲነግሩን። እድሌ ይሁን አላውቅም፣ ሆስፒታሉን በሰላም የመራሁበትን ጊዜ አላስታውስም ይላሉ ወደ ኀላፊነት ከተቀበሉበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ያለውን ፈተና እያነሱ።
አገልግሎቱ በጣም ሰፊ ነው። ጥያቄዎች የሚነሱበት፣ በርካታ አገልግሎቶች ያሉበት ታላቅ ተቋም ነው። ከባድ ቤት ነው። “ከፍም ብል ዝቅም ብል እንደዚህ የሚከብድ ተቋም አይገጥመኝም” ይላሉ ዶክተር ሃይማኖት አንጋፋውን ሆስፒታል መምራት ምን ያክል ከባድ እንደኾነ ሲገልጹ።
እንደዚህ ትልቅ ተቋም አይደለም እንጂ በሌሎች ተቋማት በኀላፊነት ሰርቻለሁ፣ እንደዚህ ግን ከባድ ተቋም አልገጠመኝም፣ እንደዚህ አይነት ተቋም ላይ የቡድን ሥራ ካልኾነ በስተቀር ብቻን መወጣት አይቻልም። ሥርዓት መዘርጋት ካልተቻለ ብቻን የማይሸፈኑ በርካታ ሥራዎች አሉ ነው የሚሉት።
በእሳቸው የመሪነት ጊዜ ሀገር አልሰከነችም። ጦርነት አላጣችም። እሳቸው ወደ ኀላፊነት እንደመጡ መከላከያ ሠራዊት የተከዳበትና ጦርነት የተቀሰቀሰበት ጊዜ ነበርና ሆስፒታሉ የሕክምና ማዕከል ነበር።
ለወትሮው አገልግሎት የሚበዛበት ሆስፒታል በጦርነቱ ወቅት ጫናው የበለጠ ከፍ አለ። በወራረው ጦርነትም ሆስፒታሉ የሕክምና መስጫ ማዕከል ነበር። ለወትሮው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖችን የሚያክመው ሆስፒታል በዚያ ወቅት ደግሞ የበለጠ ጫናው በዛበት። ያን ጊዜ ዶክተር ሃይማኖት ሲያስታውሱት “ከባድ ጊዜ ነበር” ይላሉ። ይህ ብቻ አይደለም ለዶክተር ሃይማኖት እና ለሚመሩት ተቋም ከዚህ የከፋ ከባድ ጊዜ ከፊታቸው ገጠማቸው።
የወረራው ጦርነት ተስፋፍቶ አንጋፋውን ተቋም ዘረፈ፣ አወደመ። ብዙዎች ከአምላካቸው በታች ብንታመም መዳኛችን ፈውስ ማግኛችን የሚሉት፣ የሚሳሱለትና የሚመኩበት ተቋም ሲወድም አብዝተው አዘኑ። ለዓመታት ያጠራቀማቸውን፣ ለወገኖቹ አገልግሎት የሚሰጥባቸውን መሳሪያዎች የተዘረፈውንና የወደመበትን ሆሰፒታል ማየት አሳዛኝ ጊዜ ነበር።
ዶክተር ሃይማኖት ያን ጊዜ ሲያስታውሱ “እጅግ አሳዛኝ ነበር። ከአርባ ቀን በኋላ ወደ ሆስፒታሉ ተመልሰን ስንመጣ እጅግ አሰቃቂ ነበር። እንደ ደሴ ሆስፒታል የወደመ አልነበረም” ይላሉ። በክብር የተቀበሉት እስከ መጨረሻው ድረስ አገልገሎት የተሰጠበትና የመሩት አንጋፋ ሆስፒታል በቀናት ልዩነት ውስጥ እንዳልነበር ሲኾን ዶክተር ሃይማኖት አብዝተው አዝነዋል። አዝነው ግን ዝም አላሉም። በእልህና በወኔ ሠሩ እንጂ።
በነበረው የወረራ ጦርነት እጅግ ፈታኝ ጊዜ አሳለፉ። ደሴ ከወራሪዎች ነጻ ወጥታ ወደ ሆስፒታሉ ሲገቡ እጅግ አሳዛኝ እንደነበርም ያስታውሳሉ። ግቢው ለዓመታት የቆዬ ሆስፒታል ሳይኾን የቆሻሻ መጣያ መስሎ ነበር ይላሉ ያን ጊዜ ሲያስታውሱት።
ውድመቱ የአርባ ቀን አይመስልም ነበር። አልቅሰናል፣ በርካታ መድኃኔቶችን እና የሕክምና መሳሪያዎችን አጥተናል፣ እስከመጨረሻው ድረስ የሠራ ሆስፒታል ነውና በርካታ ግብዓቶች ነበሩት ነው ያሉኝ። ይህ ጊዜ ለዶክተር ሃይማኖት እጅግ ፈታኙ ጊዜ ነበር። ተረጋግቶ ለመምራት አዳጋች ነበርና።
“ሲወድም ያዬን የተቋም ሠራተኛ በዚያ ስሜት ውስጥ ኾኖ መምራት ከባድ ነበር። በርካታ ሠራተኞች አሉ፣ ከእኔ የተሻሉ ባለሙያዎችም አሉ። ይሄን ሁሉ ለማቻቻል እና አስማምቶ ለመምራት ብዙ ነገር ይፈትናል” ነው የሚሉት። ከወረራ መልስ ወደ ተቋሙ ሲገቡ የጳውሎስ ሆስፒታል እንዲያግዛቸው ተመድቦላቸው ብዙ እገዛ እንዳደረገላቸውም ነግረውናል። ባለሙያዎች መጥተው አግዘዋቸው፣ የሕክምና መሣሪያ ሰጥተዋቸው እንደሄዱም ያስታውሳሉ። ሚዲያዎች ለደሴ ሆስፒታል የሰጡት ሽፋንም ድንቅ ነበር። የሚዲያዎች ሽፋን ሆስፒታሉ እንዲረዳ አስተዋጽኦ ነበረው።
ሙሉ ለሙሉ የወደመውን ታላቅ ተቋም የተባረኩ እጆች እንደገና አቋቋሙት፣ ዶክተር ሃይማኖትና እርሳቸው የሚመሯቸው የሆሰፒታሉ ሠራተኞች የወደመውን ሆሰፒታል አይተው አዝነው ዝም አላሉም፣ ተሰብረውም አልቆዘሙም፣ ይባስ ብሎ እልህ ያዛቸው፣ ወኔ ተናነቃቸው። በብርታት ሠሩ።
“ደሴ ሆስፒታል በምሥራቅ አማራ ብቸኛው ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ነው። የዩኒቨርሲቲም ማስተማሪያ ሆስፒታል ነው። ወሎ ዩኒቨርሲቲ እስከ እስፔሻሊስት ድረስ ያስተምርበታል። ከ60 ዓመታት በላይ እድሜ ያለው ነው። ያ ሁሉ ንብረት በዚያ ወቅት ሲወድም ያላየ የለም። በጣም ከባድ ጊዜ ነበር። ከዛ ለመነሳት እየተጋገዝን ሠራን። መንግሥት፣ ሕዝብና ድርጅቶችም አግዘውታል። ሲወድም ሕዝብ እንዳዘነለት ሁሉ ሕዝብ ደግፎታል” ብለውናል።
በችግሩ አልቆዘሙም። ለጠላት ደስ አይበለው በሚል ስሜት በትጋት ሠሩ። በአጭር ጊዜም የተሻለ ነገርን አሳዩ። በሀገራዊ ጥሪ ወደ ሀገራቸው የገቡ ዲያስፖራዎችም ድጋፍ ማድረጋቸውንም ነግረውኛል። በፌዴራልም ኾነ በክልል ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ተደግፏል። አሁን ላይ የተሻለ ቁመና ላይ ነውም ብለውናል ዶክተር ሃይማኖት። ያ ጊዜ ነገሮችን በደቂቃዎች ልዩነት እንደምናጣ ተምረንበታልም ይላሉ።
ሆስፒታሉ በወደመ ጊዜ በርካታ ታካሚዎች ያለ አገልግሎት ቆይተዋል። ” ሆስፒታሉን አጽድተን እንደገባን ታካሚዎች ወዲያው ነው የመጡት። ልክ ሲከፈት ግቢው በአንድ ጊዜ ሞላ። የሰላም ማጣት ያለንን ነገር እንዴት እንዳሳጣን አየነው። ከባድ ጊዜ ነበር። ከዛ ለመውጣት ብዙ ታግለናል። እንዲያውም አንዳንድ ነገሮች ላይ ከወትሮው በተለየ ሠርተናል። ሠራተኞች ሁሉም በወኔ ነው የተነሱት። ማግኘት ብቻ ሳይኾን ማጣት ምን እንደኾነ ስላዩት በቁጭት ሆስፒታሉን ጠርገው ገብተዋል” ነው ያሉን።
ጊዜ ሳይመርጡ፣ ደከመኝ ሳይሉ ሠሩ፣ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠየቁ፣ ለሚመጡት ሁሉ የውድመቱን ልክ ከወትሮው ጋር እያነፃፀሩ አሳዩ። የተሻለ ነገርም አደረጉ። “ያገኘናቸውን እድሎች ሁሉ በአግባቡ ተጠቅመናል፣ ያጣናቸውን እድሎች ለማግኘት እየሠራ ነው። በተገኘው አጋጣሚ ሁሉንም ነገር ለማስተካከል እየጣርን ነው” ብለዋል ዶክተር ሃይማኖት። ክልሉ ወደ ትክክለኛው መስመር መምጣት አለበት፣ ጥያቄዎቻችን በአግባቡ ማቅረብ ይገባል፣ ከጦርነት መውጣት ይገባልም ይላሉ። ያ ካልኾነ ግን አሁንም የጤና ተቋማት ይጎዳሉ፣ ተገልጋዩ ሕዝብ ይጎዳል ነው ያሉት።
ዶክተር ሃይማኖት ሆስፒታሉ የተሻለ እንዲኾን ሕልም አላቸው፣ ለዛም በብርታት ይሠራሉ። በዚያ የጦርነት ጊዜ ምንም አይነት እረፍት አልነበረንም ነው ያሉን። ጥሩ ሠርተናል፣ ሰላሙን ከሰጠን ወደፊትም ገና እንሠራለን ብለውናል። ” ከፈጣሪ ፈቃድ ጋር የማይቻል የለም፣ ያሳለፍኩት የአግልግሎት ዘመን ረጅም ነው። ከእኔ ጋር የነበሩ አሁን ከእኔ የተሻሉ ሰዎች አሉ። እኔ በመረጥኩት መንገድ እዚህ ደርሻለሁ። ከእኔ የተሻሉ ጠንካራ የሴት ጓደኞች አሉኝ። ከዚህም የተሻለ መኾን ይቻላል” ነው ያሉት ሴቶች በፈተና ወቅት ጠንካራ እንዲኾኑ ሲመክሩ።
ዶክተር ሃይማኖት የሥራ አስኪያጅነቱን ሥራ ብቻ የሚሠሩም አይደለም ጋወን ለብሰው የሕክምና አገልግሎት ይሰጣሉ። ጋወን ለብሰው እንደ ማንኛውም ሀኪም እየተንቀሳቀሱ ሲሠሩ ስላየሁ ጠየኳቸው። “ምንም ቢኾን አያስችለኝም። የምችለውን ሁሉ አግዛለሁ። ልምዱም ስላለኝ ዝም ማለት አልወድም። በሥራ ብዛት ምክንያት አንዱን ታካሚ እስከመጨረሻው ስለማልይዘው ነው እንጂ ብሠራ ውጤታማ ሥራ እሠራለሁ፣ ሀኪም ስለኾንኩ አክማለሁ። ሕግም ስለኾነ ጋወን ለብሼ ነው የምሠራው” ብለውናል።
ዶክተር ሃይማኖት ሙያውን ማወቃቸው እና በዘርፉ የረጅም ዓመታት ልምድ ማካበታቸው ለመሪነትም ጠቅሟቸዋል። ” ሙያውን አውቆ መምራት ጥሩ አጋጣሚ ነው። ትግባባለህ። ተው ስትል በሙያ ቋንቋ ይኾናል። አድርግም ስትል በሙያ ቋንቋ ይኾናል። በሌላ በኩል ሳጠፋም የሚነግሩኝን ነገር እረዳለሁ። ባለሙያ ለባለሙያ ጥሩ ነው። ዝም ብሎ ሥራ አስኪያጅ መኾን ከባድ ነው። ሙያውን ሲያውቁት ሰውን እንዴት መቆጣጠር እንደሚቻል ብቻ ሳይኾን እሱስ የሚፈልገው ምንድን ነው የሚለውን ለመለየት ያግዛል። ትንሽ ሙያ ጥሩ ነው” ብለውናል።
ታላቅ ተቋም የመሩ፣ በችግር ጊዜ የሠሩ፣ ያሠሩ በፈተና ወቅት ያልተበገሩና ያልተሰበሩ ናቸው። ሆስፒታሉን እንደቀደመው ብቻ ሳይኾን ከቀደመው የተሻለ ለማድረግ እንደሚሠሩም ነግረውናል።
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!