የደረሱ ሰብሎች ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሹ ፈጥኖ ለመሰብሰብ ርብርብ እንዲደረግ የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ አሳሰበ።

84

ደብረ ብርሃን: ጥቅምት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ2015/16 የምርት ዘመን በሰሜን ሸዋ ዞን ከ 17 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ቢታሰብም ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ችግሮች በዘርፉ ላይ ተጽእኖ አሳድረዋል።

ቀደም ሲል በሰላም እጦት፣ በዝናብ እጥረት፣ በግሪሳ ወፍ እና ቢጫ ዋግ ክስተት ምክንያት 65 ሺህ 512 ሄክታር መሬት ከምርት ውጪ ኾኗል፡፡ ከዞኑ ግብርና መምሪያ በተገኘ መረጃ መሰረትም በዚህ ምክንያት ከ90 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይታጣል።

በመምሪያው የሰብል ልማት ባለሙያ ተውልኝ ሽባባው እንዳሉት አሁን ላይ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ መጣሉ ተጨማሪ ጉዳት እንዳያደርስ ስጋት ፈጥሯል።

ከብሔራዊ ሜትሪዎሎጂ ኢንስቲትዩት በተገኘው መረጃ መሰረትም ወቅቱን ያልጠበቀው ዝናብ ሊቀጥል እደሚችልም ተመላክቷል።

ከመምሪያው በተገኘ መረጃ መሰረት የደረሱ ሰብሎችን የመሰብሰብ ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል። ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በ63 ሺህ 134 ሄክታር ላይ የተዘራ ሰብል ተሰብስቧል።

ይሁን እንጂ እንደ ጤፍ፣ ማሾ፣ ስንዴ፣ ቦለቄና መሰል የጥራጥሬ እህሎች ዝናብ መቋቋም የሚችሉ አይደሉም። ይህንን ታሳቢ በማድረግም የሚገኙ አጋጣሚዎችን በአግባቡ በመጠቀም የደረሱ ሰብሎችን በፍጥነት መሰብሰብ እንደሚያስፈልግ ባለሙያው መልእክት አስተላልፈዋል።

ይህ እንዲኾን በንቅናቄ የሚመራ ሁሉን አሳታፊ ተግባር ያስፈልጋል። በግብርናው ላይ የሚደርስ ስብራት የሁሉን ቤት ያንኳኳል ያሉት አቶ ተውልኝ ማንኛውም ሰው ሰብል ስብሰባውን እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል።

በሰብል ስብሰባ ወቅት ብክነት እንዳይደርስም ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።

ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት የምታቀርበው የኃይል ሽያጭ በየዓመቱ ጭማሪ እያሳየ ነው” የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል
Next article“ታላቅ ተቋም የመሩ፤ ለችግር ያልተበገሩ”