
ባሕርዳር፡ ጥቅምት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት የምታቀርበው የኃይል ሽያጭ በየዓመቱ ጭማሪ እያሳየ መምጣቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገለፀ።
በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ካቀረበችው የኃይል ሽያጭ 21 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር ማግኘቷም ተገልጿል።
ጅቡቲ፣ ኬንያና ሱዳን የኤሌክትሪክ የኃይል ሽያጭ የተደረገባቸው ሀገራት ሲሆኑ ለደቡብ ሱዳንና ታንዛኒያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ እየተሠራ መኾኑ ይታወቃል።
የተቋሙ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ለሱዳንና ጅቡቲ እንዲሁም ካለፈው በጀት ዓመት አጋማሽ ጀምሮ ለኬንያ የኃይል ሽያጭ እያከናወነች ትገኛለች።
የኃይል ሽያጩ በየዓመቱ እድገት እያሳየ መምጣቱን አንስተው፤ ከአምስት ዓመት በፊት ከነበረው 50 ሚሊየን ዶላር በ2015 በጀት ዓመት ወደ 101 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር ማደጉን ተናግረዋል።
ተቋሙ በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ለሱዳን፣ ለጅቡቲና ለኬንያ ከቀረበው የኃይል ሽያጭ 21 ነጥብ 4 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ማግኘቱንም ገልፀዋል።
ከሀገር ውስጥ የኃይል ሽያጭም 4 ነጥብ 38 ቢሊየን ብር ማግኘቱን አያይዘው ገልጸዋል።
የሀገር ውስጥና የጎረቤት ሀገራት የሩብ ዓመት የኃይል ሽያጭ ከእቅዱ አንፃር ሲታይ የ80 በመቶ አፈፃፀም የታየበት መኾኑንም ተናግረዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት መጨረሻ ለጎረቤት ሀገራት የሚቀርበውን የኃይል ሽያጭ 150 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ለማድረስ መታቀዱንም ተናግረዋል።
ተቋሙ በበጀት ዓመቱ ከሀገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል ሺያጭ ደግሞ 20 ነጥብ 16 ቢሊየን ብር ለማግኘት ማቀዱን አስታውቀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!