
ባሕር ዳር: ጥቅምት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አቶ ሙላት አስማማው በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የደሃና ወረዳ ቀበሌ 03 ነዋሪ ናቸው። ማር በማምረት ሥራ የቆየ ልምድ አላቸው። አካባቢያቸው ለንብ ማነብ የተመቸ መኾኑን ጠቅሰዋል። ከባለሙያዎች በሚያገኙት ድጋፍ ማርን በዘመናዊ ዘዴ እንደሚያመርቱም ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመት ከማር ምርት ብቻ 22 ሺህ ብር ገቢ አግኝተዋል። የማር ምርት በአግባቡ ለተጠቀመበት የልፋትን ዋጋ እንደማያሳጣም ይናገራሉ።
አቶ ሙላት ዘንድሮ ድርቅ መከሰቱ እና በጳጉሜን ዝናብ በመዝነቡ ለንብ የማይስማማ፣ የማር ምርትንም ሊቀንስብን ይችላል ነው ያሉት። አርብቶ አደሩ ከዘርፉ የበለጠ ተጠቃሚ እንዲኾኑም ጠንካራ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በአማራ ክልል እንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት የንብና ማር ልማት ባለሙያው አቶ መሐመድ ጌታሁን ባለፈው የምርት ዘመን ከ22 ሺህ ቶን በላይ ማር መመረቱን ተናግረዋል። ዘንድሮ ደግሞ 30 ሺህ 133 ቶን ማር ለማምረት ታቅዶ እየተሠራ ስለመኾኑ ገልጸዋል።
የተያዘው እቅድ ይሳካ ዘንድ:-
👉 ለንብ አናቢዎችና ለባለሙያዎች ሥልጠና ተሰጥቷል፤
👉 14 ሺህ ወጣቶች ተደራጅተው፣ ሠልጥነው 28 ሺህ ቀፎ ከንብ መንጋው ጋር ቀርቦላቸዋል፤
👉 120 ሺህ የሽግግርና ዘመናዊ ቀፎዎች፣ 160 ኩንታል ሰም፣ እና ሌሎች የንብ ማነቢያ ቁሳቁሶች ቀርበዋል ብለዋል አቶ መሐመድ።
በዚህ ዓመት በአብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች ለንብ ማነብ እና ለማር ምርት ምቹ ኹኔታዎች መኖራቸውንም ባለሙያው ገልጸዋል። ይህም በዓመቱ የተሻለ የማር ምርት ለማግኘት ያስችላል ነው ያሉት።
ባለፉት ዓመታት በክልሉ ከ80 በመቶ በላይ በሚኾኑ ቀበሌዎች የማር ማጣሪያ መቅረቡን ያስታወሱት አቶ መሐመድ ዘንድሮ ድርቅ ከተከሰተባቸው አካባቢዎች በስተቀር ክረምቱ ለማር ምርት ምቹ መኾኑን ገልጸዋል። ስለኾነም አናብቶ አደሩ ማርን በጥራትና በብዛት ለማምረት ከባለሙያዎች ተመካክሮ እንዲሠራ አሳስበዋል። ድርቅ የገጠማቸው አካባቢዎች ተገቢውን የማር ምርት እንዲያገኙም ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።
ከአማራ ክልል እንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት በተገኘ መረጃ መሰረት ክልሉ:-
👉 82 በመቶው ሥነ-ምህዳር ቆላና ወይና ደጋ ነው፤
👉 ሰፋፊ የተጠበቁ ተፋሰሶችና የሃይማኖት ተቋማት ደኖች አሉት፤
👉 በዚህም ውስጥ 700 ለማር ምርት የሚኾኑ የቀሰም ዕጽዋቶች አሉት፤
👉 1 ነጥብ 7 ሚሊየን የንብ መንጋ ሃብት አለው። ይህም ለማር ምርት ከፍተኛ አቅም ነው።
ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!