22 ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውን በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች መልሶ ማቋቋምና ግንባታ ፈንድ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

49

ባሕር ዳር: ጥቅምት 16/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች መልሶ ማቋቋምና ግንባታ ፈንድ ጽሕፈት ቤት በጦርነቱ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች 22 ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውን አስታውቋል።

በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተካሄደው ጦርነት መጠነ ሰፊ ጉዳት ከደረሰባቸው አካባቢዎች የአማራ ክልል አንዱ ነው። በጦርነቱ ከፍተኛ የኾነ ሰብዓዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ውድመት ደርሷል።

የአማራ ክልል በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች መልሶ ማቋቋምና ግንባታ ፈንድ ጽሕፈት ቤት፣ የአማራ ምሁራን መማክርት እና የአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም በክልሉ ላይ በደረሰው ውድመት ዙሪያ ጥናት አካሂደዋል። በጦርነቱ ከ538 ቢሊዮን ብር በላይ ውድመት እንደደረሰ በጥናቱ ይፋ መኾኑ ይታወሳል።

የደረሰው ሰብዓዊ፣ ቁሳዊ እና ሥነ ልቦናዊ ውድመት በመጽሐፍ ደረጃ በአማርኛ እና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች ታትሞ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲያውቀው ተደርጓል። ከዚህ በተጨማሪም በዌብሳይት እና አማዞን ላይ እንዲጫን መደረጉን የአማራ ክልል በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች መልሶ ማቋቋምና ግንባታ ፈንድ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አባተ ጌታሁን (ዶ.ር) ገልጸዋል።

ጽሕፈት ቤቱ በ2015 ዓ.ም ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች በመንግሥት በተመደበ አንድ ቢሊዮን ብር እንዲሁም ከዓለም ባንክ፣ ከዩ.ኤን.ዲ.ፒ እና ከግለሰቦች በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የመልሶ ግንባታ ሥራዎችን እየሠራ ነው፡፡

በጤና፣ በግብርና፣ በወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ፣ ሴቶችና ህጻናት፣ በንጹህ የመጠጥ ውኃ ግንባታ፣ በመሥኖ፣ በትምህርትና መሰል 10 ተቋማት ላይ 105 ፕሮጀክቶች ላይ እየሰራ ነው። 95 በመቶ የሚኾኑት የፕሮጀክት ሥራዎች ተጠናቅቀዋል ነው ያሉት።

ቅድሚያ ተሰጥቶ ከተሠሩ ተቋማት ውስጥ ደግሞ ትምህርት አንዱ ነው። በበጀት ዓመቱ በ332 ሚሊዮን ብር በሰባት ዞኖች እና በሦስት ከተሞች ላይ 22 ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ደግሞ 95 በመቶ ተጠናቅቀዋል ተብሏል።

ከትምህርት ቤት ግንባታ ባለፈ የትምህርት ግብዓት ማሟላት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ዋና ዳይሬክተሩ ነግረውናል። ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር 41 ሺህ ወንበሮችን በተለያዩ ትምህርት ቤቶች የማሰራጨት ሥራ እየተሠራ ይገኛል።

ለአራት መምህራን ኮሌጆች ደግሞ ኮምፒውተር የማሟላት ሥራ መሠራቱን በማሳያነት አንስተዋል። ከዚህም ባለፈ 14 የምርምር ተቋማት እንዲሁም ለ11 የጤና ተቋማት ደግሞ የሥራ ፈጠራ ማዕከል ተሠርቷል ተብሏል።

በዚህ ዓመትም የክልሉ መንግሥት አንድ ቢሊዮን ብር መመደቡን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ሌሎች ረጂ ድርጅቶችን እና ማኅበረሰቡን በማስተባበር ከባለፈው ዓመት በተሻለ መንገድ የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ሥራ እንደሚሠራ ገልጸዋል።

በጦርነቱ የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለማቋቋምና ለመገንባት በተለይም ደግሞ የነገውን ሀገር ተረካቢ ትውልድ እጣ ፈንታ ወሳኝ የኾነውን የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች፣ በውጭ እና በሀገር ውስጥ የሚኖር ኢትዮጵያዊ የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል።

በተለይም ደግሞ አዳሪ እና ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ላይ ትኩረት አድርገው ቢሠሩ በክልሉ ከሚገኙ አዳሪ ትምህርት ቤቶች የተገኘውን ውጤት ማስፋት እንደሚቻል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየፋይናንስ ማኅበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም ሊያስቀጥል መኾኑን የአማራ ክልል ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ገለጸ።
Next article“በምርት ዘመኑ 33 ሺህ 133 ቶን ማር ለማምረት አቅዶ እየሠራን ነዉ” የአማራ ክልል እንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት