የፋይናንስ ማኅበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም ሊያስቀጥል መኾኑን የአማራ ክልል ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ገለጸ።

46

ባሕር ዳር: ጥቅምት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የፋይናንስ ማኅበራዊ ተጠያቂነት ዜጎች መንግሥት የሚሠራው ልማት በሕጉና በእቅዱ መሠረት መከናወኑን የሚገመግሙበትና ማኅበራዊ ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚተገበር ፕሮጀክት ነው።

በአማራ ክልል ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ የፋይናንስ ማኅበራዊ ተጠያቂነት ፕሮጀክት አስተባባሪ ምስጋናው ስሜነህ የፋይናንስ ማኅበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም ሊጀመር መኾኑን ገልጸዋል።

ፕሮግራሙ መንግሥት ማኅበራዊ ልማቶችን ምን ያህል እንዳሳደገ እና ዜጎችም ምን ያህል ፍላጎታቸው እንደተሟላ የሚገመግሙበት አሠራር ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ መንግሥታዊ ባልኾኑ ድርጅቶች በ73 ወረዳዎች ለ10 ዓመታት ሲከናወን መቆየቱን አስተባባሪው ጠቅሰዋል። ከታሕሳስ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ወደ መንግሥት ፕሮግራምነት እንደሚዛወር ገልጸዋል።

ከ2014 ዓ.ም ጀምሮም በዳንግላ ወረዳ በሙከራ ትግበራ ሲፈጸም መቆየቱን አቶ ምስጋናው ተናግረዋል። በትግበራውም በልማት ሥራዎች ውጤታማነትም ኾነ በማኅበረሰቡ አዎንታዊ ምላሽ መገኘቱን ገልጸዋል።

የፋይናንስ ማኅበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም ከጎጥ ጀምሮ በየደረጃው የሚዋቀር ኮሚቴ የሕዝቡን የልማት ፍላጎት ቅደም ተከተል አውጥቶ ለመንግሥት የሚቀርብበት አሠራር መኾኑንም አቶ ምስጋናው ገልጸዋል።

ፕሮግራሙ ሕዝብ የልማት ወጪንም በመጋራትና ተሳትፎን በማጎልበት የልማት ባለቤትነትንም የሚያሳድግ። የዜጎችን የመጠየቅ አቅም በማጎልበት በመንግሥትም ላይ ተጠያቂነትን የማስፈን ዓላማ እንዳለውም ገልጸዋል። የልማት ፍትሐዊነትን እንደሚያሰፍን እና የዴሞክራሲ እሴትንም እንደሚያጎለብት አብራርተዋል።

የተተነተነ የሕዝብ ልማት ፍላጎት መረጃ እስካለ ድረስ በመንግሥት የአቅም ውስንነት ያልተመለሰ የልማት ፍላጎት ቢኖር እንኳ መንግሥታዊ ያልኾኑ የልማት አጋሮች የሚሠሩበትን ዕድል እንደሚያሳድግም ተገልጿል።

ፕሮግራሙ ከሙከራ ትግበራ አልፎ በሰፊውና በሙሉ ጊዜ ሲሰራ ሕብረተሰቡ በልማት ተጠቃሚ ከመኾኑም በተጨማሪ የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለማዳበርም አቅም እንደሚሆን ነው አቶ ምስጋናው ያመላከቱት።

ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበፊፋ ፕሬዚዳንት ላይ የቀረበው ክስ ተዘጋ፡፡
Next article22 ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውን በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች መልሶ ማቋቋምና ግንባታ ፈንድ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።