በፊፋ ፕሬዚዳንት ላይ የቀረበው ክስ ተዘጋ፡፡

22

ባሕር ዳር: ጥቅምት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የስዊዘርላንድ ዐቃቢ ሕግ የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ያላግባብ በመጠቀም ፣ መንግሥታዊ ምስጢሮችን አሳልፎ በመስጠት ወንጀል ጠርጥሮ ያቀረበውን ክስ መዝጋቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

የስዊዝ ዐቃቢ ሕግ እንዳለው ከግለሰቦች እና ከድርጅቶች የቀረበለትን የሰነድ መረጃ አንብቧል፡፡ የምስክሮችን ቃልም ተቀብሎ በቴክኖሎጂ የታገዘ ምርመራ አድርጓል፡፡ በመጨረሻም “ክሱ በተሳሳተ ዕይታ የቀረበ ጥርጣሬ መኾኑን አረጋግጫለሁ” ብሏል፡፡

ዐቃቢ ሕግ ሃንስ ሞሬር እና ዑልሪች ዌደር “በኢንፋንቲኖ ላይ የቀረቡትን ክሶች ‘ውድቅ’ አድርገው መዝገቡን መዝጋታቸውን ዋሽንግተን ታይምስ ጋዜጣ በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡

ኢንፋንቲኖ በበኩላቸው መጀመሪያውንም ክሱ የተሰነዘረብኝ ስሜን ለማጠልሸት ነው ሲሉ ሽንጣቸውን ገትረው መቃወማቸውን አስታውሰዋል፡፡ ውሳኔውም ለእኔ እና ለፊፋ ድል ነው ካሉ በኋላ ምንጊዜም የፊፋንና ሕሊናዊ ሕጎችን አክብረው እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

እ.ኤ.አ በ2015 የአሜሪካ አቃቤ ሕግ የኤፍ.ቢ.አይ የምርመራ ግኝትን ተከትሎ በርካታ የፊፋ ከፍተኛ መሪዎች በጉቦ ቅሌት ክስ ተመስርቶባቸው ነበር፡፡

በዚህም መሰረት የቀድሞ የፊፋ ፕሬዚዳንት ሴፕ ብላተር እና ምክትል ፕሬዚዳንት ሚሼል ፕላቲኒ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ፓውንድ ለሥልጣናቸው ማቆያ በመክፈላቸው ጥፋተኛ ተብለው ሥልጣናቸውን እንዲለቁ መገደዳቸው አይዘነጋም፡፡

ዘጋቢ፡- ሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሕዝቡ ልጅና ጠባቂ ነው” ዶክተር ለገሰ ቱሉ
Next articleየፋይናንስ ማኅበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም ሊያስቀጥል መኾኑን የአማራ ክልል ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ገለጸ።