“የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሕዝቡ ልጅና ጠባቂ ነው” ዶክተር ለገሰ ቱሉ

69

ባሕርዳር፡ ጥቅምት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያውያንን ኅብረ ብሔራዊነት በሚያንጸባርቅ መልኩ የተደራጀ፣ የሕዝብ ልጅና ጠባቂ መኾኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ገለጹ፡፡

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የተመሠረተበት 116ኛ ዓመት በዓል በመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ክቡራን ሚኒስትሮችና ሠራተኞች በተገኙበት በተደረገ የፓናል ውይይት ተከብሯል፡፡ በሥነ ሥርዐቱ ማጠቃለያ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የአገልግሎቱ ሚኒስትር ክቡር ዶ.ር ለገሰ ቱሉ “በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ሚኒስቴር ተቋማት ሲመሠረቱ የመከላከያ ሠራዊቱ አብሮ የተመሠረተበትን ቀን መነሻ በማድረግ ጥቅምት 15 ቀን የሠራዊቱ ቀን ተደርጓል” ብለዋል፡፡

ክቡር ሚኒስትሩ እንዳብራሩት ሠራዊቱ በተለያዩ ሥርዓቶች ሀገርንና ሕዝብን ለመጠበቅ ኃላፊነቱን ሲወጣ የነበረ ቢሆንም የሥርዐቶቹ ጠባቂ ተደርጎ ይቀረጽ እንደነበረ አስታውሰው ከለውጡ ማግሥት በሕገ መንግሥቱ መሠረት ከፖለቲካ ውግንና ገለልተኛ ሆኖ ከመላዉ ኢትዮጵያውያን የተውጣጣ ብዝኃነት ያለዉ ተደርጎ መደራጀቱን አስታውሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሠራዊት የሥርዐት ጠባቂ ተደርጎ በመቈጠሩና በተለይም ኢሕአዴግ ወደሥልጣን ሲመጣ መበተኑ ሀገሪቱን ክፉኛ እንደጎዳትና የአየር ኃይሉን ጨምሮ ልዩ ልዩ የሠራዊቱን ክፍል አዳክሞት እንደነበረ ክቡር ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

ከለውጡ ማግሥት ግን ሕገ መንግሥቱን፣ ዓለማቀፋዊ ወታደራዊ ሳይንሱንና የኢትዮጵያን ነባራዊ ኹኔታ መሠረት አድርጎ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዐት መጠበቅ እንዲችል ተደርጎ መደራጀቱን ገልጸዋል፡፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ድኤታ ክቡር አቶ ከበደ ዴሲሳ በበኩላቸው በመርሐ ግብሩ መክፈቻ ባደረጉት ንግግር “የሠራዊቱ ቀን ጥቅምት 15 እንዲከበር መደረጉ በዐዋጅ የተመሠረተበትን መነሻ ያደረገ፣ በመደመር ዕሳቤ መሠረት ከነበረ ወረት ላይ የመጨመርና የተቋም ቀጣይነትን ለማረጋገጥ የሚደረገዉ ጉዞ ማሳያ ነው” ብለዋል፡፡

የክቡር ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አቶ ዝናቡ ቱኑ ደግሞ የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት ታሪክና የሠራዊት ቀንን ጥቅምት 15 ቀን ለማክበር ያስለገበትን ታሪካዊ ዳራ የዳሰሰ የመወያያ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡

በቀረበዉ ጽሑፍ ዙሪያ የአገልግሎቱ ሠራተኞች ገንቢ አስተያየቶችን ሰጥተዋ፡፡ በተለይም የሠራዊቱን ጥንተ መሠረት መነሻ በማድረግ ቀኑ መከበሩ ተገቢ እንደኾነ አስተያየት ተሰጥቷል፡፡ ሠራዊቱ ሕይወቱን እየገበረ ሀገር ሲጠብቅ በዚህ መልኩ ሕዝብ ምስጋና የሚያቀርብበትና ዕውቅና የሚሰጥበት ቀን መኖሩ ተገቢ እንደኾነም ተነሥቷል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleስፔናዊ ግብ ጠባቂ ዴቪድ ደሃያ ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ ሊመለስ ነው፡፡
Next articleበፊፋ ፕሬዚዳንት ላይ የቀረበው ክስ ተዘጋ፡፡