“መንገድ ሲዘጋና ሰላም ሲጠፋ የመጀመሪያው ተጎጅ የጤና ተቋም ነው” የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል

78

ደሴ: ጥቅምት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሰላም እጦት ባለ ጊዜ የጤና ተቋማት ከፍተኛ ጫና ይገጥማቸዋል። ሕሙማንም ወደ ጤና ተቋማት ሄደው አገልግሎት ለማግኘት ይቸገራሉ። መዳን እየቻሉ በመንገድ መዘጋት ወይም በመድኃኒት አቅርቦት ምክንያት ያልፋሉ። የጤና ባለሙያዎችም የድካማቸውን ፍሬ ሳያገኙ ይቀራሉ።

በአማራ ክልል በነበረው የወረራ ጦርነት ምክንያት በርካታ የጤና ተቋማት ወድመዋል፣ ተዘርፈዋል። ከወደሙት የጤና ተቋማት መካከል የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አንዱ ነው። አንጋፋው ተቋም ለዓመታት ያካበተውን ሃብቱን ተዘርፎ እና እንዲወድም ተደርጎ ባዶውን ቀርቶ ነበር።

የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ሃይማኖት አየለ ጦርነት ለጤናው ዘርፍ ትልቅ እንቅፋት ነው፤ ሆስፒታል ከምንም ተፅዕኖ ውጭ ኾኖ ሥራውን ሲሠራ መልካም ነው ብለዋል።

ሆስፒታል ሰብዓዊ ተቋም ነው፤ ከምንም ነገር ተጽዕኖ ተላቆ ሁሉንም እያከመ ነው መኖር ያለበትም ይላሉ። መንገድ ሲዘጋ መድኃኒት አይመጣም፤ አንቡላንሶች ለተሻለ ሕክምና የሚደርሱ ታካሚዎችን እንደፈለጉ መውሰድ አይችሉም ብለዋል።

የጤና ተቋማት ከሚሰጡት ሕክምና በተጨማሪ የተሻለ ቦታ ለማድረስ ከፍተኛ ችግር እንደሚያጋጥማቸውም ተናግረዋል። መንገድ ተዘጋ ሲባል ሕዝብ ይጨነቃል ያሉት ዶክተር ሃይማኖት የህክምና ክትትል የሚያደርጉ ታካሚዎች ተጨማሪ መድኃኒት ስጡኝ እያሉ እንደሚያስቸግሩም ገልጸዋል።

በየአንድ ወር ልዩነት መድኃኒት የሚወስዱ ታካሚዎች መንገድ ሊዘጋ ነው በሚል የሥድስት ወር ስጡን እያሉ እንደሚያስቸግሯቸውም ነግረውናል። ነገ የሚመጣው ነገር ያስፈራቸዋል፤ ትንሽ ኮሽ ባለ ቁጥር የሚጎዳው የጤና ተቋም ነውም ብለዋል።

በሰላም እጦት ምክንያት ግብዓት እንደ ልባቸው እየመጣላቸው አለመኾኑንም ገልጸዋል። የሰላም እጦት ሲኖር የመድኃኒት ዋጋ እንደሚንርም ተናግረዋል። በሆስፒታሉ ውስጥ መድኃኒት ሲጠፋ ከሆስፒታሉ ውጭ ባሉ መድኃኒት ቤቶች በሦስት እና በአራት እጥፍ ዋጋ እንደሚጨምርም ተናግረዋል። ይህ ደግሞ ታካሚዎችን በእጅጉ ይጎዳቸዋል። መንገድ ሲዘጋና ሰላም ሲጠፋ የመጀመሪያው ተጋላጭ የጤና ተቋም መኾኑንም አስረድተዋል።

ከባለፈው ችግር ሳንወጣ ሌላ ችግር እንዳይመጣ እንሰጋለንም ብለዋል። በሰላም እጦት ምክንያት ከክልሉ ዋና ከተማና ከሀገሪቱ ዋና ከተማ ጋር ለመገናኘት ፈታኝ መኾኑንም አንስተዋል። እገዛ ከሚያደርጉላቸው የጤና ቢሮና የጤና ሚኒስቴር ባለሙያዎች ጋርም በሰላም እጦት ምክንያት አለመገናኘታቸውን ነው የተናገሩት። ማኀበራዊ ተቋማት ከግጭትና ከጫና ነፃ መኾን አለባቸውም ብለዋል። ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ በአጭሩ ካልተቋጩ የጤና ተቋማት በእጅጉ እንደሚጎዱም ተናግረዋል።

የአማራ ክልል በጦርነቱ ምክንያት ከባድ ጊዜ ማሳለፉን ያስታወሱት ዶክተር ሃይማኖት ለሌላ ችግር ላለመጋለጥ መጠንቀቅ ያስፈልጋል ብለዋል። እንቅስቃሴ ሲቆም ዋጋ ይጨምራል ሕዝብም ይሰቃያል ነው ያሉት። አገልገሎት መስጫ ተቋማት ተረጋግተው መሥራት እንደሚቸገሩም ገልጸዋል። በግጭት ሕዝብ ተጎጅ እንደሚኾንም ተናግረዋል።

በሆስፒታል ውስጥ በመሣሪያ የሚተነፍሱ፣ ምጥ የተያዙ እናቶች እና ሌሎች ይኖራሉ የሚሉት ዶክተር ሃይማኖት እነዚህን ለማከምና ለማገልገል የተረጋጋ ሰላም ያስፈልጋል ብለዋል። ሰላም ማጣትን ማስቆምና ሕዝብ እንደፈለገ መንቀሳቀስ እንዲችል ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ዶክተር ሃይማኖት በየጊዜው ለሚፈጠሩ ችግሮች የጋራ መፍትሔ ማበጀት ይገባልም ብለዋል። ክልሉ ወደኃላ እየተመለሰ ነው ያሉት ዶክተር ሃይማኖት የሰላም እጦቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ መስተካከል አለበት፤ ወገኖቻችንም ማጣት የለብንም ነው ያሉት።

“ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ከተቻለ ወገኖቻችንን በሰላም እናስተናግዳለን” ብለዋል። ሁሉም ለሰላም በር መክፈት እንደሚገባውም ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሰዎች ለእናንተ ሊያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው”
Next articleስፔናዊ ግብ ጠባቂ ዴቪድ ደሃያ ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ ሊመለስ ነው፡፡