“ሰዎች ለእናንተ ሊያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው”

35

ባሕር ዳር: ጥቅምት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በማንኛውም ኅብረተሰብ ውስጥ የእያንዳንዱ ሰው ድርጊት የሚገመገምበት ግብረገባዊ እሴት አለ። እሴቶቹ በነባራዊ ኹኔታዎች አስገዳጅነት የተፈጠሩ እንጂ በሰዎች ነፃ ምርጫ የተገኙ አይደሉም። የሰው ልጅ ማንነቱን የሚያንፀውና አካሉን የሚገነባው በምግብ እና በሳይንሳዊ ዕውቀቶች ብቻ ሳይኾን በእነዚህ ግብረገባዊ እሴቶችም ነው። ይህ ግብረገባዊ እሴት በሚገባ ካልተያዘ ከባሕሉ እና ከእሴቱ የወጣ ሰውን ይፈጥራል፡፡

ለመኾኑ አኹን ላይ ግብረገብነትን ማኅበረሰቡ በምን ያክል መጠን ይረዳዋል? የሚለውን ለመፈተሽ አሚኮ ሰዎችን ለማነጋገር ሞክሯል፡፡

አሚኮ ያነጋገራቸው አዛውንቱ አቶ ወርቁ ዋለ እና ወጣት ምንታምር ቢኾነኝ ግብረገብ ሙሉ በሙሉ የለም ለማለት ባይቻልም ግን ከቀን ወደ ቀን እየተሸረሸረ እንደሄደ ነግረውናል፡፡

በሰዎች ዘንድ አኹን ላይ ለራስ ከማሰብ ወጥተው ለሰው ማሰብ የሚባል ነገር እየጠፋ እንደሄደም ነው የሚገልጹት፡፡ ግብረገብ ያለው ማኅበረሰብ ይፈጠር ዘንድም ማኅበረሰቡ ከላይ እስከታች መሥራት እንዳለበት ይገልጻሉ፡፡

በግበረገብ ላይ የተለያዩ ጥናቶችን ያካሄዱና በሀሳቡ ላይ መጻሕፍትን የጻፉት የግብረገብ ምሁር ሺበሺ አለባቸው (ዶ.ር) እንደሚሉት ግብረ ገባዊ እሴቶች በመማር እና በመላመድ የሚገኙ እንጂ በተፈጥሮ አብረው የሚወለዱ አይደሉም ብለዋል።

የአንድ ሀገር ዜጋ ግብረገባዊ እንዲኾን መሠረቱ ቤተሰብ ላይ የተመሠረተ ነው ባይ ናቸው፡፡ አንድ ወላጅ ለልጁ የሚሰጠው ወይም የሚያሳየው ቤተሰባዊ መስመር እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ ለሚያከናውናቸው ሥራዎች ትልቅ መሠረት እንደሚጥልም ገልጸዋል፡፡ በተለይ አንድ ልጅ እስከ ሰባት ዓመቱ የሚይዘው የግብረገብ ትምህርት 95 በመቶ በሕይወቱ ላይ እንደሚተገበር እና በኋላ ለመቀየርም እንደሚቸገር ነው የሚገልጹት፡፡

አንድ ሰው በጎልማሳነት ደረጃ ከደረሰ በኋላ በግብረገብ ላይ ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው 5 በመቶ ብቻ ስለመኾኑም ነው የነገሩን። ዶክተር ሺበሺ “ልጅህን ስጠኝ እና እንደፈለከው አደርግልሃለሁ” የሚለው የሥነ ልቦና ትምህርት ወላጆች ለልጆች መልካም ግብረ ገብ ማበልጸጊያ መሠረቶች ማሳያ እንደኾነም ነው የገለጹት፡፡

በመንፈሳዊ አስተምህሮም “ልጅህን ቅጣው ፤ አድጎ እንዳያሳዝንህ” የሚለው መንፈሳዊ መልእክት መኖሩን ተናግረዋል። ቅጣው ሲል መልካምነትን በማስተማር እንጂ ልጆችን በመደብደብ፣ በመቆጣት እና በማስፈራራት እንዳልኾነ ጠቁመዋል፡፡

ግበረገብነትን ከታች ከመዋለ ሕጻናት ጀምሮ በሰፊው መሥራት ወሳኝ መኾኑን ያነሱት ምሁሩ ልጆችን የሚያስተምሩ መምህራን ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡

ከዓለም አቀፋዊነት ጋር ተያይዞ የሚሰራጩ ነገሮችና ከሰብዓዊነት ይልቅ ለገንዘብ ትኩረት መስጠት ለሥነ ምግባር መሸርሸር ምክንያት እንደሚኾኑም ነው የነገሩን፡፡

ቤተሰብ ፣ የመንግሥት ተቋማት፣ የትምህርት ተቋማት እና ቤተ እምነቶች ደግሞ ግብረገባዊ እሴቶችን እና ሕግጋትን በመቅረጽ እና በመተግበር፣ በማክበር እና በማስከበር፣ በማወቅና በማሳወቅ፣ በመረከብ እና በማስተላለፍ ረገድ ከፍተኛ ሚና ያላቸው ማኅበራዊ ተቋሞች በመኾናቸው ጠንክረው ሕጻናት ላይ መሥራት አለባቸው ነው ያሉት።

በመንግሥት በኩልም ሀገራዊ የኾኑ የግብረገብ እሴቶችን በሥርዓተ ትምህርት በማካተት መስጠት እንደሚገባውም ነው ያስገነዘቡት፡፡ ሥርዓተ ትምህርቱም ሲቀረጽ ምሁራን በትኩረት መርምረው አካታች በኾነ መንገድ ሁሉም ሊተገብረው የሚችል መኾን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ቤተ እምነቶችም ዜጎችን በሃይማኖታዊ ሥነ ምግባር የማነጽ ግዴታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

“ሰዎች ለእናንተ ሊያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው” የሚለው ሥነ መለኮታዊ መርሕ እንዲከበር ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም ነው ያሳሰቡት፡፡

ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሻለቃ የሠራዊት ቀንን አከበረ።
Next article“መንገድ ሲዘጋና ሰላም ሲጠፋ የመጀመሪያው ተጎጅ የጤና ተቋም ነው” የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል