
ባሕር ዳር: ጥቅምት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በምዕራብ ጎጃም ዞን የሚገኘው የይልማና ዴንሳ ወረዳ አዴት ከተማ ለሳምንታት የዘለቀ የሰላም እጦት ውስጥ ገብታ እንደነበር ነዋሪዎች አስታውሰዋል። በዚህም ግጭት ሰበብ በከተማ አሥተዳደሩ ውስጥ የሚገኙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ ውድመት መድረሱን ጠቁመዋል። “የሰላም እጦት ችግሩ በንብረት እና በሰው ሕይወት ላይ ኪሳራ አድርሶ ነው ያለፈው” ብለውናል ያነጋገርናቸው ነዋሪ።
አሁን ላይ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ ኀይሎች ወደ አካባቢው በመግባት ለሕዝቡ ሰላም እየሠሩ ስለመኾኑም ነዋሪዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። የመንግሥት የጸጥታ ኀይሎች ወደ ቦታው ከገቡ በኃላ የከተማዋ ሰላም መመለሱንም ጠቅሰዋል። ሙሉ በሙሉ ተዘግተው የነበሩት ሱቆች እና ሌሎችም የገበያ ቦታዎች አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ ክፍት ኾነው አገልግሎት እየሰጡ ነው ተብሏል።
በከተማዋ የሚገኙ ባንኮች ተከፍተው እየሠሩ ነው። ተዘግቶ የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎትም አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ ክፍት ኾኖ ሕዝቡ እየተገለገለ ነው ብለዋል ነዋሪዎች።
የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ተፈጥሮ የነበረው ግጭት ዳግም እንዳይከሰት እና ዘላቂ ሰላም እንዲጸና ከመንግሥት የጸጥታ ተቋማት ተወካዮች ጋር ተከታታይ ውይይቶችን እያደረጉ ስለመኾኑም ተገልጿል።
በከተማው ውስጥ የሚገኙ የንግድ ተቋማት ተከፍተው ሰላማዊ የኾነ የሰዎች እንቅስቃሴ ቢኖርም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ግን አሁንም ድረስ እንደተዘጉ ናቸው ተብሏል። የመንግሥት ተቋማት የወደሙ በመኾኑ ቢከፈቱም ሙሉ አገልግሎት ለመስጠት አዳጋች ነው ሲሉም ነዋሪዎች ገልጸዋል።
“ግጭቱ የሕዝብን ሀብት ከማውደም የዘለለ ፋይዳ አልነበረውም” ያሉት ነዋሪ ሁሉም ለሰላም መቆም እንዳለበት መክረዋል። የወደሙ ተቋማት በትብብር ተተክተው መንግሥታዊ አገልግሎት በፍጥነት እንዲጀመርም ነዋሪዎች ጠይቀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!