
ባሕር ዳር: ጥቅምት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከጸኑት የጸናች፣ በጠላት ያልተደፈረች፣ ጠላቶቿን ሁሉ ድል የመታች፣ የገፏትን ሁሉ የጠላች፣ ጦር የመዘዙባትን፣ ጎራዴ የሳሉባትን ሁሉ ያንበረከከች፣ በልጆቿ ጀግንነት ለዘመናት በድል የተሞሸረች፣ በአሸናፊነት የተከበረች፣ በድል አድራጊነት የተረማመደች፣ በጠላቶቿ ፊት ግርማና ሞገስን ያገኘች፣ በወዳጆቿ የተወደደች፣ መመኪያና መኩሪያ የኾነች ጹኑ ሀገር።
ለግጭት የሰለሏት ያውቋታል፣ ጦር ያዘመቱባትን ድል አድርጋቸዋለች እና ይረዷታል። ሲገፏት እየጣለቻቸው፣ ሲዘምቱባት እየገረሰሰቻቸው፣ በኀይሏ ድል እየመታቻቸው፣ የመጡበትን ጎዳና እያስጠፋችባቸው መልሳቸዋለችና ሳይወዱ በግዳቸው ያከብሯታል፣ እየራዱ እና እየተንቀጠቀጡ ይፈሯታል፣ የእጅ መንሻ እየያዙ ይመጡላታል፣ ፎክረው መጥተው አልቅሰው ይመለሱባታል፣ እየደነፉ ተነስተው እጅ ይነሱላታል።
ልጆቿ በነፃነት የኖረችውን፣ በክብር የሚውለበለበውን ሰንደቅ አስቀድመው ይገሰግሳሉ፣ ድል አድርገው በድል ይመለሳሉ። አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሰንደቅ በቀደመበት፣ የኢትዮጵያ ልጆች በዘመቱበት ሁሉ ድል አለ፣ በገሰገሱበት ሁሉ አሸናፊነት አለ። ያለ ድል የተመለሱበት ዘመን የላቸውም። ሰንደቁ የማይደፈር ነውና። ዘመናቸው በድል ያሸበረቀ፣ ታሪካቸው በአሸናፊነት የደመቀ ነው።
ነፃነቷን ያስከበረች ሀገር የድል ቀኗን ታከብራለች፣ ጠላቶቿን የገረሰሰች ምድር በነፃነት ትኖራለች፣ ድንበሯን የጠበቀች ሀገር የአሸናፊነት ታሪኳን ትዘክራለች፣ ማንም እንዳልደፈራት ለልጆቿ ትነግራለች፣ እስከ ወዲያኛው እንዳትደፈር እንዲጠብቋት ለተተኪ ልጆቿ ቃል ኪዳን ትሰጣለች። ብዙዎች ነፃ የወጡበት ቀን ያከብራሉ፣ ከባርነት የተለዩበትን ዘመን ይዘክራሉ፣ ከጨለማ የተላቀቁበትን ቀን ያስታውሳሉ።
ኢትዮጵያ ግን በነፃነት የኖረች፣ ለማንም በምንም ያልተደፈረች ሀገር ናትና የነፃነት ሳይኾን የድል ቀኗን ታከብራለች፣ ጠላቶቿን ሁሉ የደመሰሰችበትን ጊዜ ጀግና ነኝ ስትል ታስታውሳለች። ደግመው ለመነሳት ያሰቡትን ሁሉ አትችሉኝም ትላቸዋለች፣ በግፍ አትዘምትም፣ በግፍ የዘመቱባትንም አታረማምድም። ጋራዋ አያረማምድም፣ ልጆቿም ስንዝር ሙሉ አያላውሱም። እርሷ ከሌሎቹ ትለያለች፣ ከሌሎቹም ትበልጣለች፣ ከሌሎቹም ተለይታ በረቀቀ ቀለም በታሪክ መዝገብ ላይ ሠፍራለች፣ ከሌሎችም ልቃ በማያረጅ ብራና ተቀርፃለች፣ በማይናወጽ ዓለት ላይ ተፅፋለች። ጥቁሮች ሁሉ እናታችን ይላሉ፣ ወራሪዎች ሁሉ ስሟን በሰሙ ጊዜ አንገታቸውን ይደፋሉ፣ ሽንፈታቸውን እያስታወሱ ይቆዝማሉ።
ዓለምን ያናወጸው የቅኝ ገዢዎች ክንድ አላናወፃትም፣ የግፍ ግፍ የሠራው የፋሽሽት ሤራ አላንበረከካትም፣ ኀያላን ነን የሚሉት አመጽና ሁካታ አልሠበራትም፣ እርሷ ጽኑ ሀገር ናትና ጩኸት አይጥላትም፣ በዓለት ላይ የተመሠረተች ናትና ገፍተው አያናዉጿትም። ከተከበረችበት የክብር ዙፉን ላይ አያወርዷትም፣ እርሷ በፈተና ትጸናለች፣ በመከራ ትበረታለች፣ የማይቻል የሚመስለውን ትችላለች፣ ወዮላት አበቃች፣ ደቀቀች ስትባል ጠላቶቿን አድቅቃ ትነሳለች፣ ያጠፏታል የተባሉትን ሁሉ ታጠፋቸዋለች፣ ያንበረክኳታል የተባሉትን ሁሉ ታንበረክካቸዋለች፣ አይቻሉም የተባሉትን ሁሉ እንዳልነበር ታደርጋቸዋለች። ኢትዮጵያ ጀግኖችን የወለደች፣ በጀግኖቿም ስትጠበቅ የኖረች ታላቅ ሀገር ናት።
ጳውሎስ ኞኞ የኢትዮጵያን እና የኢጣልያን ጦርነት በከተቡበት መጽሐፋቸው ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ ለሺህ ዓመታት ያህል የተደጋጋመ ሙከራ ተደርጓል። ኢትዮጵያዊያን ግን ሀገራቸውን በሌላ በአድ ሳያሲዙ ባላቸው ኃይል ሲከላከሉ ቆይተዋል። በአውሮፓም ኾነ በኢሲያ ወይም በአፍሪካ የሚነሱ ታላላቅ መንግሥታት ጉልበት እያገኙ ግዛታቸውን በሚያሳፉበት ጊዜ ኢትዮጵያንም ለመደረብ ብዙ ጊዜ ሞክረዋል። ኢትዮጵያዊያን ግን ለማንም ሳይበገሩ እስካሁን ሀገራቸውን አስከብረው ቆይተዋል። ኢትዮጵያን አስገብሮ ለመያዝ በተደጋጋሚ የውጭ ጦር ቢመጣም ኢትዮጵያውያን ባላቸው ኀይል የማይበገሩ ኾነው የሚመጣውን የውጭ ጦር ሁሉ መልሰዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያን አበውና እመው በጸሎታቸው፣ ጀግኖቹ በክንዳቸው፣ በላባቸው ፣በደማቸው ፣በአጥንታቸው ፣በከበረች ሕይወታቸው ሲጠብቋት ኖረዋል ፣ወደፊትም ይጠብቋታል። ኢትዮጵያ የወታደርን ቀን እያከበረች ነው። ወታደር ለኢትዮጵያ ልዩ ቦታ አለው። አበው በጸሎታቸው ሁሉ በዳር በድንበር ቆሞ ሀገር የሚጠብቀውን ጠብቅልን፣ አፅናልን፣ አበርታልን እያሉ ይጸልዩለታል። ኢትዮጵያዊያንም በልባቸው ያስቡታል፣ በአንደበታቸው ያደንቁታል፣ አስተማማኝ ደጀን ይኾኑታል። ሀገራቸውን የሚጠብቅላቸው፣ ከጠላት የሚከላከላቸው፣ ሰንደቃቸውን በኩራት የሚያውለበልብላቸው፣ ከፍ ከፍም የሚያደርግላቸው ነውና እየቆረሱ ያጎርሱታል፣ እየቀዱ ያጠጡታል፣ ያስከብራቸዋልና ያከብሩታል።
” ከዚያው ማርልኝ ያን ወታደር፣
ከዚህ እንዳይመጣ ይጠብቃል ሀገር” እያሉ የሚመኙለትና ለሀገሩ በተሰዋ ጊዜ አምላክ ነፍሱን እንዲምርለት የሚማፀኑለትም ብዙዎች ናቸው። የፅኑ ሀገር ፣ ጀግና ወታደር ቀኑን እያከበረ ነው። ይች ቀን ጀግኖች የሚታሰቡባት፣ ለዘመናት ኢትዮጵያን በደምና በአጥንታቸው ያጸኑ የቁርጥ ቀን ልጆች የሚታወሱባት ቀን ናት።
የጸናች ሀገር ጀግና ወታደር አላት። የጸናች ሀገር ፅኑ ሕዝቦች አሏት። ከጠላት የሚከላከሏት፣ በመከራ ዘመን የሚያበረቷት፣ መከራውን የሚያሻግሯት፣ ጨለማውን የሚገፉላት፣ በብርሃንም የሚመሉላት። ወታደር ለኢትዮጵያ ከምንም ከማንም በላይ ነው። ወታደር ኢትዮጵያን ከአምላኳ ቀጥሎ ይጠብቃታል፣ ማንም እንዳይደፍራት ይከላከልላታል፣ በኢትዮጵያ ላይ በግፍ እግራችንን እናነሳለን ያሉትን ሁሉ ይቀጣላታል፣ እየቀጣም አደብ ያስይዝላታል።
የኢትዮጵያ ወታደር ጀግና ነው ጠላት የማይደፍረው፣ ብርቱ ነው መከራ የማይሰብረው ጽኑ ነው፣ እሾህና አሜካላ የማያስቆመው፣ ከግስጋሴው የማያስቀረው ኀያል ነው። የኢትዮጵያ ወታደር ኢትዮጵያዊያን የወለዱት፣ ኢትዮጵያዊያን የሚያከብሩት፣ ሰንደቃቸውና ሀገራቸውን እንዲጠብቅላቸው አደራ የሰጡት ፣የሚመኩበት ፣የሚኮሩበት ነው። በአንድነት የሚጠብቃቸው ፣በአንድነት ደጀን የሚኾኑት ፣ምልክቱ ሰንደቅ የኾነ፣ ሰንደቅ ማስከበር ፣ሀገር በክንዱ የሚያኖር ነው። ጀግናው ወታደር የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያዊያን ነው።
የፅኑዋን ሀገር ጀግና ወታደር ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይኾኑ አፍሪካውያን ጭምር ይኮሩበታል። ይመኩበታል፣ በቸገራቸው ጊዜ ይጠሩታል፣ በጠሩትም ጊዜ ፈጥኖ ይደርስላቸዋል። ከጭንቅና ከችግር ይታደጋቸዋል።
በክንዱ ብርታት ያበረታቸዋል። የፅኑ ሀገር ጀግና ወታደር፣ የፅኑ ሕዝብ ድንቅ መከታ፣ የታላቅ ሀገር ኀያል ወታደር። በደምና በአጥንታችሁ ለዘመናት ሀገር ስትጠብቁ ለኖራችሁ፣ ፅኑ ሀገርንም ላወረሳችሁ፣ ዛሬም በደምና በአጥንታችሁ ሀገር እየጠበቃችሁ ላላችሁ ሁሉ ክብር ይድረሳችሁ። መልካም የጀግኖች ቀን ይሁንላችሁ።
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!