የግሪሳ ወፍን ለመከላከል የሁለተኛ ዙር በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት ተጀመረ፡፡

35

ባሕር ዳር: ጥቅምት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ሁለተኛው ዙር የግሪሳ ወፍን ለመከላከል የሚደረገው በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት መጀመሩን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ከነሐሴ 3/2015 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል በተለያዩ አራት ዞኖች የግሪሳ ወፍ ተከስቶ ጉዳት እያደረሰ መኾኑን አሚኮ በተለያዩ ዘገባዎች አስቃኝቷል፡፡

በኦሮሚያ ብሔረሰብ አሥተዳደር የደዋ ጨፋ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ሰብል ልማት ቡድን መሪ ወይዘሮ እናት አሠፋ በወረዳው በ9 ቀበሌዎች የግሪሳ ወፍ መከሰቱን ተናግረዋል፡፡

በወረዳው በሦስት የግሪሳ ወፍ ማደሪያ ቦታ በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት መካሄዱንም ጠቁመዋል፡፡በወረዳው በሁለቱ ዙር ርጭት ከ2 ሚሊዮን 500 ሺህ በላይ የግሪሳ ወፍ መወገዱን ተናግረዋል፡፡

የአርሶ አደሮች እገዛም የተሻለ መኾኑን ወይዘሮ እናት ተናግረዋል፡፡

የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አበበ ጌታቸው በዞኑ ድጋሚ በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት መካሄድ መጀመሩንም ተናግረዋል፡፡

በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች ላይ የተከሠተውን የግሪሳ ወፍ ለመከላከል እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል፡፡

በዞኑ 31 ቦታዎች ላይ የግሪሳ ወፍ ማደሪያ ቦታዎች ተለይተዋል ያሉት ቡድን መሪው ራቅ ያሉ ቦታዎችን ጨምሮ ለመሸፈን እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡

ሸዋሮቢት ላይ ያለው አውሮፕላን ማረፊያ ለመጠቀምም ጽዳት እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡እስካኹን የኬሚካል እጥረት እንዳላጋጠመም ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሮችም በሥራው ላይ በንቃት እየተሳተፉ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሮች ርጭት በሚካሄድበት አካባቢ እስከ 15 ቀን እንስሳትን ባለማሠማራት እና ግጦሽ ባለማጨድ ኀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት፡፡

እንዲኹም ጭስ በማጨሥ ለአውሮፕላኑ ምልክት ለማሳየት የሚደረገው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል እና ወፉ ከደረሱ ሰብሎች ላይ እንዳያድር የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር አግደው ሞላ በአማራ ክልል ሁለተኛው ዙር በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

በተለያዩ ቦታዎች በተደረገ ርጭትም የግሪሳ ወፍ መከላከል መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡ አርሶ አደሮችም ቦታ የመለየት እና ምልክት የመሥጠት ሥራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር የእፅዋት ጥበቃ እና መሪ ሥራ አሥፈጻሚ በላይነህ ንጉሴ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በደቡብ ኢትዮጵያ የግሪሳ ወፍ መከሰቱን እና ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል፡፡

የግሪሳ ወፍን ለመከላከል በአማራ ክልል ሁለተኛው ዙር በአውሮፕላን የታገዘ ኬሚካል ርጭት መካሄድ መጀመሩንም ጠቁመዋል፡፡

የዘንድሮው የግሪሳ ወፍ ባልተለመዱ ቦታዎች ኹሉ እንደተከሰተ ተናግረዋል፡፡

የግሪሳ ወፍን ለመከላከል ከአንድ ሺህ ሊትር በላይ ኬሚካል ጥቅም ላይ መዋሉን አንስተዋል፡፡

በዚኽም ከ50 ሚሊዮን በላይ ወፎችን ማጥፋት መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡

ሥራው በዚህ ከቀጠለ በጥቂት ቀን ችግሩን በቁጥጥር ሥር ማዋል እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡

አንዳንድ ቦታዎች ለርጭት የማይመቹ በመኾናቸው አርሶ አደሮች ወፎችን በመረበሽ የማባረር ሥራውን አጥብቆ ሊሠራ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleባሕር ዳርን ከወልቂጤ ከተማ የሚያገናኘው ጨዋታ ተጠባቂ ነው፡፡
Next article“ጽኑ ሀገር፤ ጀግና ወታደር”