
ባሕር ዳር: ጥቅምት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በአራተኛ ሳምንት መርሐ ግብር ቀን 9 ሰዓት ሀዋሳ ከተማን ከኢትዮጵያ መድን ያገናኛል፡፡
በሦስት ሳምንታት ጨዋታዎች አምስት ነጥብ የሰበሰቡት ሀዋሳዎች አንድ ጨዋታ ብቻ አሸንፈዋል፡፡ በአንጻሩ በሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። ቡድኑ በመጀመሪያው ሳምንት በፋሲል ከነማ ሦስት ግብ አስተናግዷል፡፡ ይሁንና በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ግብ ያላስተናገደ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል አለው።
በሌላ በኩል በሁለት ጨዋታዎች ያስቆጠሩት አንድ ግብ መኾኑ የአጥቂውን ክፍል ደካማናነት የሚያሳይ ነው፡፡
በሦስት ጨዋታዎች ድል፣ አቻና ሽንፈት ያስመዘገቡት ኢትዮጵያ መድኖች በአራት ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
መድኖች ወላይታ ዲቻን በገጠሙበት ጨዋታ ከቀደመው ብቃታቸው ወርደው ነው የታዩት። የግብ እድል መፍጠርም ሲሳናቸው ተስተውለዋል፡፡ ታዲያ በአዲስ የማጥቃት ጥምረት ጨዋታውን ይጀምራሉ ተብለው የሚጠበቁት አሠልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ተጋጣሚያቸው ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ያለው ቡድን እንደመኾኑ የአጥቂዎቻቸውን ስልነት ከፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ሁለቱ ክለቦች እስካሁን 27 ጊዜ ተገናኝተዋል። ሀዋሳ 13 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነትን አስመዝግቧል፡፡ በ10 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ መድን 4 ጨዋታ አሸንፏል። በግብ ረገድ ሀዋሳ 36 እንዲሁም መድን 26 ግቦችን አስቆጥረዋል።
ምሽት ባሕር ዳር ከተማ ከወልቂጤ ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ በጉጉት የሚጠበቅ ነው፡፡ ወልቂጤዎች የጨዋታ መሻሻል ማሳየታቸው፣ በሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት አለማስተናገዳቸው የብርታታቸው ማሳያ ይኾናል እየተባለ ነው፡፡
ከጨዋታ ጨዋታ ኳስን ተቆጣጥሮ የሚጫወት ቡድን የገነባው አሠልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረት በዛሬው ጨዋታ ዕድሎችን ወደ ግብ የመቀየር ችግር ያለበት ቡድን ማሻሻያ ማድረግ ግድ ይለዋል፡፡
በአንጻሩ ተጋጣሚያቸው ባሕርዳር ከተማ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ያለው መኾኑ ወልቂጤዎችን ሊከብዳቸው እንደሚችል እሙን ነው፡፡
ከሦስት ጨዋታዎች አራት ነጥብ የያዙት የጣና ሞገዶቹ በሊጉ ድል፣ አቻና ሽንፈትን አስመዝግበዋል።
ባሕርዳር ከተማ በፈጣን ሽግግር ለማጥቃት የሚሞክር ጠንካራ የአጥቂ ክፍል አለው፡፡ በየጨዋታውም በአማካይ ሁለት ግቦችን ማስቆጠራቸው የማጥቃት ብቃታቸውን የሚያሳይ ነው።
ቡድኑ ምንም እንኳ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ቢኖረውም አማካይ ክፍሉ በቂ ሽፋን ይሰጠዋል ማለት እንደማይቻል ሶከር ኢትዮጵያ ዘግቧል። ወልቂጤ እና ባሕር ዳር ስድስት ጊዜ ተገናኝተዋል። ባሕር ዳር ሁለት ጊዜ ሲረታ ወልቂጤ ደግሞ ሁለቱን አሸንፏል ፤ ሁለት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። በአምስቱ ጨዋታዎች ባሕር ዳር ከተማ ዘጠኝ ግቦች ሲያስቆጥር ወልቂጤዎች ደግሞ አምስት ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል።
ትናንት ቀን ዘጠኝ ሰዓት በተደረገ ጨዋታ ሲዳማ ቡና ሻሸመኔ ከተማን 3 ለ 1 ረትቷል፤ በምሽት 12 ሰዓት ጨዋታ ደግሞ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድሬዳዋ ከተማን 3 ለ 2 ማሸነፉ ይታወሳል፡፡
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!