“አፍሪካ ከቅኝ ተገዥነት ቀንበር እንድትላቀቅ የጀግናው የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ጉልህ ሚና ተጫውቷል” የአውሮፓዊው የታሪክ ጸሐፊ

65

ባሕር ዳር: ጥቅምት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ መሪ የነበሩት ግርማዊ ቀዳማዊ ዓጼ ኀይለሥላሤ እ.ኤ.አ በ1924 የአውሮፓን ሀገራት በተለይም ፈረንሳይን እየጎበኙ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ታዲያ ስምንተኛው ዓለም አቀፍ የኦሎምፒክ ጨዋታዎች በፓሪስ ከተማ እየተካሄደ ነበር፡፡ እሳቸውም በሚቀጥለው የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ መሳተፍ እንድትችል በማቀድ በመስፈርቶቹ ዙሪያ የዓለም አቀፉን የኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ፒየር ደ ኩበርቲን አስጠርተው ጠየቁት፡፡

ይሁንና የኦሎምፒክ ኮሚቴዉ ፕሬዚዳንት “ኢትዮጵያ ስፖርተኛ የት ታገኛለች?” ሲሉ ለግርማዊነታቸው ጥያቄ አቀረቡ። ንጉሡም “ስፖርተኞችን ከጦር ሠራዊታችን እንመርጣለን” አሏቸውና በመርሕ ደረጃ ተስማሙ፡፡ በዚህም መሰረት ስፖርተኞችን ከጦር ሠራዊት አባላት ተመረጡና ልምምድ በጃን ሜዳ እንዲሠሩ ተደረገ፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥትም በ1928 በአምስተርዳም በሚካሄደው ዘጠነኛው የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ እንድትሳተፍ ለኮሚቴው በይፋ ማመልከቻ ጻፈ፡፡ይሁንና አዲስ የተመረጡት የዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ቤልጀማዊው ፕሬዚዳንት ሄንሪ ባይሌት-ላቱር “ኢትዮጵያን በኦሎምፒክ ጨዋታዎች ማሳተፍ ማለት ጦርነት በአውሮፓ ላይ ማወጅ ነው” ማለታቸውን የታሪክ ምሁሩ ሚሼል ሲክስ ጽፈዋል፡፡ ነገር ግን ለዐይን መመለሻ እንዲኾን “የአፍሪካ ሀገራትን በጨዋታዎች ላይ ለመሳተፍ አቅም የላቸውም” በሚል ውድቅ አደረጉት፡፡

ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ሀገራት ጋር መሳ ለመሳ በኦሎምፒክ ጨዋታዎች መወዳደር እችላለሁ ፤ ለዚህ ደግሞ ብቁና ንቁ ስፖርተኞችን ከጦር ሠራዊቴ እመለምላለሁ ማለቷን የዓለም ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ፒየር ደ ኩበርቲን በፈረንሳይ የተለያዩ ጋዜጦች ላይ በማተማቸው የአውሮፓን ሀገራት መሪዎች በተለይ የጣሊያን መሪዎች ሳያስኮርፍ እንዳልቀረ የታሪክ ምሁሩ አትተዋል።

የኾነው ኾኖ አውሮፓውያን እየመረራቸውም ቢኾን የኢትዮጵያ ዘመናዊ ስፖርት በጀግንነት፣ በድል አድራጊነት፣ በአልበገርም ባይነት፣ በአካል ብቃት እና በሥነ ምግባር ከሚታወቁት ከጦር ሠራዊቱ መፍለቁን ተረዱ፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በአውሮፖው ሀገራት መሪዎች ምላሽ ቢያዝንም ዘመናዊ ስፖርትን ጦር ሠራዊቱ በየቦታው እንዲስፋፋ አቅጣጫ ተሰጠ፡፡ የታሪክ ምሁሩ ሚሼል ሲክስ በ20ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ እንዳሉት አፍሪካ ከቅኝ ተገዥነት ቀንበር እንድትላቀቅ የጀግናው የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡

በዚህ አኩሪ ታሪክ ምክንያትም በአፍሪካ ደረጃ ዘመናዊ አትሌቲክስ ሲታሰብ የኢትዮጵያ ስም ቀድሞ ይመጣል። በስፖርቱ ውስጥ ደግሞ በፊት አውራሪነት የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ሲታወስ ይኖራል ሲሉ የታሪክ ምሁሩ ሚሼል በእማኝነት ጽፈዋል።

116ኛውን የሠራዊት ቀን “በተፈተነ ጊዜ ሁሉ የሚፀና የድል ሠራዊት” በሚል መሪ ሐሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል፡፡

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል በ2015/16 የምርት ዘመን ከ75 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በጥጥ ሰብል መሸፈኑን ግብርና ቢሮ ገለጸ።
Next articleባሕር ዳርን ከወልቂጤ ከተማ የሚያገናኘው ጨዋታ ተጠባቂ ነው፡፡