በአማራ ክልል በ2015/16 የምርት ዘመን ከ75 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በጥጥ ሰብል መሸፈኑን ግብርና ቢሮ ገለጸ።

79

ባሕር ዳር: ጥቅምት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የምርምር ተቋማት ምርታማ፣ በሽታ ሊቋቋሙ የሚችሉ እና በኢንዱስትሪ ተፈላጊ የጥጥ ዝርያዎች ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩም ቢሮው አሳሰቧል።

በአማራ ክልል ለኢንዱስትሪ ጥሬ እቃነት በስፋት ከሚመረቱ ሰብሎች መካከል ጥጥ አንዱ ነው። ምዕራብ ጎንደር፣ ማዕከላዊ ጎንደር፣ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ፣ ምዕራብ ጎጃም ዞኖች እና በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ደግሞ በስፋት የሚመረትባቸው አካባቢዎች ናቸው።

በ2014/15 የምርት ዘመን 82 ሺህ 442 ሄክታር መሬት በጥጥ ተሸፍኖ ከ1 ሚሊዮን 135 ሺህ በላይ ኩንታል የጥጥ ምርት እንደተገኘ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት ዳይሬክተር አግደው ሞላ ነግረውናል።

ዳይሬክተሩ እንደገለጹት በ2015/16 የምርት ዘመን ደግሞ 102 ሺህ 740 ሄክታር በማልማት ከ2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ጥጥ ለማግኘት ታቅዶ ነበር። ይሁን እንጅ ከታቀደው ውስጥ መሸፈን የተቻለው 75 ሺህ 645 ሄክታር መሬት ብቻ ነው።

በባለፈው የምርት ዘመን የነበረው የጥጥ የገበያ ችግር የተሻለ የገበያ ተፈላጊነት ባላቸው ሌሎች ምርቶች መሸፈኑ ለእቅዱ አለመሳካት በምክንያትነት ተቀምጧል።

የምርት ዘመኑን የቅድመ ምርት ትንበያ እየተሠራ መኾኑንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የገበያ ችግር ለኢንዱስትሪ ምርቶች መሠረታዊ ችግር መኾኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ በዚህ ወቅትም በክልሉ ከተከሰተው የጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ በገበያ ትስስር ላይ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ ለመሥራት መቸገራቸውን ገልጸዋል።

ከገበያ ችግር ባለፈ የዝርያ ችግር ሌላኛው ለጥጥ ልማቱ ፈተና እንደኾነ ተነስቷል። የምርምር ተቋማት ምርታማ፣ በሽታ ሊቋቋሙ የሚችሉ እና በኢንዱስትሪ ተፈላጊ ዝርያዎች ላይ ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ጥጥ ተረካቢዎችም ምርቱ በዘላቂነት እንዲመረት ከአምራቾች ጋር በመቀራረብ በተሻለ ዋጋ መግዛት እንዲችሉ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የጥጥ ምርት እንዳይባክን እና ጥራቱን ጠብቆ ለኢንዱስትሪዎች እንዲቀርብ የሚመለከው ሁሉ ሊሠራ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ዐጼ ምኒልክ የጦር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ያቋቋሙበት ቀን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ቀን ኾኖ እንዲከበር ተደርጓል” ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
Next article“አፍሪካ ከቅኝ ተገዥነት ቀንበር እንድትላቀቅ የጀግናው የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ጉልህ ሚና ተጫውቷል” የአውሮፓዊው የታሪክ ጸሐፊ