“ዐጼ ምኒልክ የጦር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ያቋቋሙበት ቀን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ቀን ኾኖ እንዲከበር ተደርጓል” ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

131

ባሕር ዳር: ጥቅምት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በ116ኛ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ቀን አከባበር ላይ ንግግር አድርገዋል። ፊልድ ማርሻሉ ኢትዮጵያ ረጅም ዕድሜ ያላት ቀደምት እና በትውልድ ቅብብሎሽ የዘለቀች ታላቅ ሀገር መኾኗን ገልጸዋል።

በእነዚህ ረጅም የታሪክ ዘመናትም በየትውልዱ በነበሩ ልጆቿ ተጋድሎ ነጻነቷ እና ክብሯ ተጠብቆ የተላለፈችልን ሀገር ናት ብለዋል።

መንግሥት በተለወጠ ቁጥር የሀገር እሴቶች እየፈረሱ በመሄዳቸው ቀደምት ጀግኖች እና ባለድሎች እየተዘነጉ፣ ተተኪው ትውልድም የጀግንነት እና የአርበኝነት ሞዴል እንዳያገኝ የሚያደርጉ ፖለቲካዊ እሳቤዎች ሲያጋጥሙን ቆይተዋል ነው ያሉት።

በተለያዩ ጊዜያት ወደ ሥልጣን በመጡ መሪዎች እሳቤ ላይ ብቻ ተመስርተው ሲጻፉ የነበሩ ታሪኮች የጭቅጭቅ እና የግጭት መንስዔ ስለመኾናቸውም ተናግረዋል።

ትውልድ በጋራ የተግባባበት የጋራ ታሪክ ባለመኖሩ በአንድነት ቆሞ ሀገሩን ከመገንባት ይልቅ ገዥዎች በሚሰጡት አጀንዳ ጎራ ለይቶ ለመናቆር ተገዷል ብለዋል።

ለአብነትም በፊት ይከበር የነበረው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ቀን የቀደምት ጀግኖችን ታሪክ ቆርጦ ያስቀረ እና የረሳ ነበር ነው ያሉት። ከለውጡ በኋላ በተደረሰው ውሳኔ መሠረት ቀኑ ታሪክን አካታች በኾነ መልኩ እንዲከበር ኾኗል ነው ያሉት ፊልድ ማርሻሉ።

የመከላከያ ሠራዊት ቀን የሚከበርበትን ወቅት ለመምረጥ ጥናት ስለመደረጉም ገልጸዋል። በዚህም መሠረት በዘመናዊ የመንግሥት አሥተዳደር ውስጥ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በቋሚነት ተደራጅቶ እንደተቋም የተመሠረተበትን ቀን የሠራዊት ቀን በዓል ለማድረግ ተመራጭ ኾኖ ተወስዷል ነው ያሉት።

በዚህም መሠረት “ዐጼ ምኒልክ የጦር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ያቋቋሙበት እና ሚኒስትር የሰየሙበት ቀን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ቀን ኾኖ እየተከበረ ነው” ብለዋል ፊልድ ማርሻሉ።

ይህ ታሪካዊ ቀን ጥቅምት 15/1900 ዓ.ም ነበር። ለዚህም ነው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ቀን በየዓመቱ ጥቅምት 15 እንዲኾን የተወሰነው ብለዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ቀን በዚህ ታሪካዊ ቀን መከበሩ ቀደምት ጀግኖችን ሞዴል ያደረገ፣ ከቀደምቶች ታሪክ የሚማር እና የሀገር አለኝታ የኾነ ሠራዊት ለመገንባት ስለማስቻሉ ፊልድ ማርሻሉ አመላክተዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያ ፈተናን ወደ ድል የሚቀይር የአሸናፊ ሠራዊት ባለቤት ናት” የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
Next articleበአማራ ክልል በ2015/16 የምርት ዘመን ከ75 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በጥጥ ሰብል መሸፈኑን ግብርና ቢሮ ገለጸ።