“ኢትዮጵያ ፈተናን ወደ ድል የሚቀይር የአሸናፊ ሠራዊት ባለቤት ናት” የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

50

ባሕርዳር፡ ጥቅምት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ፈተናን ወደ ድል የሚቀይር የአሸናፊ ሠራዊት ባለቤት ናት ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ለ116ኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

ሙሉ መልዕክቱ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

መላው ኢትዮጵያዊያን እንኳን ለ116ኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን አደረሳችሁ!

በዛሬው ዕለት 116ኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ነው፡፡ ጥቅምት 15 ቀን 1900 ዓ/ም በኢትዮጵያ ታሪክ ልዩ ስፍራ አለው፡፡ ዕለቱ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ተቋማዊ መልክ ተላብሶ በሚኒስቴር ደረጃ የተመሰረተበት ቀን ነው፡፡ ኢትዮጵያ 116 ዓመታትን ያስቆጠረ፤ በትውልድ ቅብብሎሽ ፀንቶ የቆየና ሀገርን ያፀና የመከላከያ ተቋም ባለቤት መሆኗ ዛሬ ላይ ለጠንካራ ተቋማት ግንባታ ትልማችን እንደ ወረት የሚወሰድ በጎ የታሪካችን አካል በመሆኑ እለቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ይዘከራል፡፡

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከተመሠረተበት ከዛሬ 116 ዓመት በፊት ጀምሮ የአያት ቅድመ አያቶችን ወኔ፣ የሀገር ፍቅርና ጀግንነት ተላብሶ በፅናት ቀጥሏል፡፡ በደም መስዋዕትነት በተጻፈው አኩሪ ታሪኩ ሀገርን እየታደገ ዛሬ ላይ የደረሰው መከላከያ ሠራዊታችን፤ ምንግዜም ቢኾን ቃል ኪዳኑ እናት ሀገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት፡፡ መከላከያ ሠራዊታችን አንድ ክፍለ ዘመን በተሻገረ ታሪኩ ሀገር አፅንቷል፣ ሉዓላዊነታችንን አስከብሯል፣ የግዛት አንድነታችንን አስጠብቋል፣ በደምና አጥንቱ ኢትዮጵያን ከትውልድ ወደ ትውልድ አሸጋግሯል፡፡

መከላከያ ሠራዊታችን በዘመናት መካከል ኢትዮጵያ ላይ የሚደቀኑ ፈተናዎችን በፅናትና በጀግንነት እየተሻገረ የሚያሸንፍ ድል አብሳሪ ሠራዊት ሆኖ ዛሬም ቀጥሏል፡፡ የኢትዮጵያ ጀግኖች ዘመናዊ የውትድርና ስልጠና ሳያገኙና ዘመናዊ መሳሪያ ሳይታጠቁ በወቅቱ እጅግ የተደራጀውን የወራሪ ኃይል በአድዋ ድል አድርገው ለቀጣይ ትውልድ ነፃ ሀገርን አስረክበዋል፡፡ በፋሽስት ጣልያን ወረራ ወቅት ራሳቸውን ‟ጥቁር አንበሳ” በሚል ስያሜ አደራጅተው ለአምስት ዓመታት በዱር በገደሉ ሲዋደቁ የነበሩት የኢትዮጵያ አርበኞች ሀገራቸውን ለድል አብቅተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መከላከያ ሠራዊታችን በካራማራ ተራራ ወራሪውን ኃይል በመምታት ዳር ድንበራችንን አስከብሯል፡፡

ከውስጥም ሆነ ከውጭ የኢትዮጵያ ኅልውና ላይ አደጋ የደቀኑ ኃይሎችን በሙሉ በተለያዩ ጊዜያት በጥንካሬ በመዋጋት ክቡር መስዋዕትነት የከፈለውም ይኸው ለዘመናት ሲገነባ የመጣው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ነው፡፡

ከሀገር ውስጥ አልፎ ዝናው በዓለም የናኘው መከላከያ ሠራዊታችን፤ በኮሪያ፣ በኮንጎ፣ በሩዋንዳ፣ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን፣ በሶማሊያና በሌሎችም ሀገራት የሰላም ማስከበር ግዳጆቹን በብቃት በመወጣት የጀግነታችን ምልክትና የኩራታችን ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል፡፡

በመሆኑም ከጥንት እስከ ዛሬ የሉዓላዊነታችን ዋስትና፣ የኩራታችን ምንጭ፣ የፈተና ጊዜ የመጨረሻ ምሽግ የሆነውን የመከላከያ ሠራዊት ቀንን በሃገር አቀፍ ደረጃ ማክበር ጀግናው መከላከያ ሠራዊታችንን ማክበር ነው፡፡

ዛሬም እንደ ትላንቱ በየቦታው ከሚንቀሳቀሱ የጥፋት ኃይሎች ጋር በመፋለም ሀገሩን እያፀና፤ የሕዝብንም ሰላም እያስጠበቀ የሉዓላዊነት ዋስትና፣ የክፉ ቀን ምሽጋችን ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ቅዠታቸውን እውን ለማድረግ ከዛሬ አሻግረው ነገን የማያስቡ ፅንፈኞች የጀግናውን መከላከያ ሠራዊታችን ስም በሀሰት ለማጠልሸት ዘወትር ያለ እረፍት ቢተጉም ሰራዊታችን ለእናት ሀገሩ የገባውን ቃል ኪዳን በልቡ አኑሮ በዚህች ሰዓትና ደቂቃ ሳይቀር በየጦር ሜዳው ለሃገሩ ተጋድሎ እያደረገ ነው፡፡

መከላከያ ሠራዊታችን ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን በመጠበቅ፣ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን በመፋለም፣ ዳር ድንበርን በማስከበር በሰማይም ኾነ በምድር ኢትዮጵያችንን ቀን ለሊት ፈተናዋን እያሻገረ፤ ሞቷንም እየሞተላት ነው፡፡

በመሆኑም ኹሉም ኢትዮጵያዊ የመከላከያ ሠራዊት አባላት የሚከፍሉትን ታላቅ መስዋዕትነት በመገንዘብ የተለመደውን ጠንካራ ደጀንነቱን አጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል፡፡ በየተሰማራንበት የሥራ ገበታ እንደ መከላከያ ሠራዊት አባላት ሁሉ በወኔ፣ በትጋትና በፅኑ የሀገር ፍቅር ስሜት ልንሠራ ይገባል፡፡

በተፈተነ ጊዜ ኹሉ የሚፀና የድል ሠራዊት!

ክብር ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት!

Previous article“መከላከያ የሰላም ኃይል ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next article“ዐጼ ምኒልክ የጦር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ያቋቋሙበት ቀን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ቀን ኾኖ እንዲከበር ተደርጓል” ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ