
ባሕር ዳር: ጥቅምት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)116ኛው ዓመት የሀገር መከላከያ ሠራዊት በዓል “በተፈተነ ጊዜ ሁሉ የሚፀና የድል ሠራዊት” በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ ነው፡፡
በበዓሉ ላይ ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የጦር ኀይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) መከላከያ ማለት ማንዴላን ያሠለጠነ፣ ሙጋቤን ያስደመመ፣ ከሱዳን እስከ ሊቢያ፣ ከኩባ እስከ ላይቤሪያ በመከራ ተፈትኖ በድል የጸና ሠራዊት ማለት ነው ብለዋል፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የጦር ኀይሎች ጠቅላይ አዛዡ በንግግራቸው የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት በጦር ሜዳ ከሚያስመዘግበው ጀግንነት በላይ የኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን የሰላም አምባሳደር ነው ብለዋል፡፡ ሰላም አስከባሪ የኾነው ሠራዊት አጥንቱን የሚከሰክሰው ደሙንም የሚያፈሰው በሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ነው ያሉት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የጦር ኀይሎች ጠቅላይ አዛዥ ያለንን ሰላም ለማጽናት፣ የጠፋ ሰላምን ለመመለስ እና የመጣ ሰላምን ለማጽናት ውድ የሚባል ዋጋ ይከፍላል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወታደር 116 ዓመታትን ያስቆጠረ እና መሠረት ያለው ተቋም ነው ያሉት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የጦር ኀይሎች ጠቅላይ አዛዡ መሠረቱን የሚያውቅ ሀገሩንም ታሪኩንም ያጸናል ብለዋል፡፡ ጠንካራ እና ዘመናዊ ሠራዊት የገነቡት ቀደምቶቻችን ታላቅ እንደነበሩ በእናንተ ማየት ይቻላልም ነው ያሉት፡፡ ሰላም ለማስከበር ከሀገር ወጥቶ አርሶ አደር የሚያግዝ፣ ትምህርት ቤት የሚገነባ እና የጤና ተቋማት ገንብቶ የሚያስረክብ ታላቅ ሠራዊት ባለቤቶች ናችሁም ብለዋል፡፡
ሠራዊቱ ዘመኑን የዋጀ፣ የሚፈጥን እና የሚፈጥር እንዲኾን ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሪፎርም ተሠርቷል፡፡ ሪፎርሙ አስተሳሰብ፣ አደረጃጀት እና የማድረግ አቅም ያለው ኀይል መገንባት ላይ ያተኮረ እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው አንስተዋል፡፡ በአየር ኀይል፣ በምድር፣ በባሕር እና በሳይበር የተደራጀው ሠራዊት ትናንትን፣ ዛሬን እና ነገን እንዲያንሰላስል ተደርጎ ተሠርቷል ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከኢትዮጵያ ያነሰ ዓላማ የለውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ መያዝ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ በማንም ኀይል ተሸንፋ አታውቅም ወደፊትም አትሸነፍም፤ ኢትዮጵያ ማንንም ወርራ አታውቅም የመውረር ፍላጎት የላትም ፤ መከላከያ እንደ ስሙ ሥራው መከላከል እንጂ ማጥቃት አይደለም፤ መከላከያ ከምንም በላይ የሰላም ኀይል ነው ብለዋል፡፡
ከሠራን እና ከተጋን መለወጥ የምትችል ሀገር እንዳለችን አይተናል ያሉት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የጦር ኀይሎች ጠቅላይ አዛዡ ማንኛውም ፈተና ኢትዮጵያን ያስተምራል፣ ይሠራል እንዲሁም ኢትዮጵያን ያጸናል እንጂ ወደ ኃላ አያስቀራትም ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!