
ባሕር ዳር: ጥቅምት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)“በተፈተነ ጊዜ የሚፀና ሠራዊት” በሚል መሪ መልእክት 116ኛው የመከላከያ ሠራዊት ቀን አከባበር ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስተር እና የጦር ጠቅላይ አዛዥ አቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ባስተላለፉት መልእክት መከላከያ የጠፋን ሰላም ለማምጣት የሚተጋ ፤ ያለን ሰላም ለማስጠበቅ የሚታትር ፤ ለሉአላዊነት መሥዋዕትነት የሚከፍል የሀገር ዘብ የኩራት ምንጭ ነው ብለዋል።
መከላከያ ከአፍሪካ እስከ ኮሪያ በዘመተበት ሁሉ የኩራት፣ የኅብረት እና የልማት ምልክትም ኾኖ ቀጥሏል ነው ያሉት። ይህን አሠራር በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲቀመጥ ለማድረግ ሪፎርም እንደተደረገም አስረድተዋል። ሪፎረሙ አንደኛው በእሳቤ ሁለተኛው በትጥቅ ሲኾን ሦስተኛው ደግሞ የማድረግ አቅም ያለው እንዲኾን ማስቻል እንደኾነ ነው ያስገነዘቡት፡፡
መከላከያ የብልጽግና ፓርቲ ሳይኾን የሀገር እንዲኾን አድርገናል። መከላከያ አሰላለፉና ትጥቁ በምድር ብቻ ሳይኾን በባሕርም ፣በአየርም የተደራጀና የታጠቀ እንዲኾን ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት። መከላከያ ሰልፍ የሚያካሂድ ብቻ ሳይኾን ውጊያ የሚያቅድ ውጊያ የሚመራ እና የሚተገብር የአፍሪካ ብሎም የምሥራቅ አፍሪካ ኩራት ስለመኾኑም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በማንም ተሸንፋ አታውቅም ፤ ኢትዮጵያ ወራም አታውቅም አትወርም ፤ መከላከያ መግደል ማበላሸትን ማጥፈትን መሰረት አድረጎ አያውቅም አያጠፋም ፤ መከላከያ የተለያቱ ሀገሮች ሰላም አስከባሪ ኾኖ ሠርቷል ፤ አሁንም ሰላም አሰከባሪ ኾኖ ይቀጥላል ብለዋል።
“ኢትዮጵያ የልማት ሀሳቦች ስታነሳ ልትወር ነው የሚል ሃሳቦች ሲነሱ እንመለከታለን ይህ ስህተት ነው ፤ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር በጋራ መልማት እንጂ የመውረር ፍላጎት የላትም ፤ በሰላም በድርድር እንጂ በግዳጅ በመውረር የምናሳካው ፍላጎት የለውም” ብለዋል። እኛ ውጊያ ገጥመን ተሸንፈንም ፣ ተንበርክከንም አናውቅም ፤ ታሪካችን የሚያሳየን ማሸነፍን ፣ ማንበርከክን ነው ፤ ይሁን እና በመውረር የምናሳካው ፍላጎት እና ልማት የለም ሲሉም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን የተሻለች አድርገን ለቀጣዪ ትውልድ ለማስረከብ እንሠራለን ሊያቆመን የሚችል አንዳች ኀይል የለም ብለዋል” የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስተር እና የጦር ኀይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)።
ዘጋቢ፡- አንዷለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!