
ባሕር ዳር: ጥቅምት 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ኢትዮጵያ በተፈተነችበት ወቅት ሁሉ ፈተናዋን ፈተናው አድርጎ የተጋፈጠ፤ ድል ባደረገች ጊዜ ሁሉ የድሏ ምስጢር ምሰሶ የኾነ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በዘመናቷ መካከል ሁሉ አላት፡፡
የዓለም ጥቁር ሕዝብ የድል ተምሳሌት ኢትዮጵያ ሽንፈትን የማያውቅ እና ከሰብዓዊነት የማይርቅ ሠራዊት ከገነባች እነኾ 116ኛ ዓመታትን አስቆጠረች፡፡
ኢትዮጵያ ከአንድ ምዕተ ዓመት በተሻገረው የዘመናዊ ሠራዊት ግንባታ ታሪኳ ከዓድዋ እስከ ማይጨው፤ ከምፅዋ እስከ ካራማራ በድል የደመቀ፣ በሥነ- ምግባር የታረቀ፣ በደም እና በአጥንት የረቀቀ ሠራዊት ገንብታለች፡፡ ከራሱ በላይ ሀገሩን፤ ከነፍሱ በላይ ስሙን የሚወድ የምድራችን ጀግና ሰራዊት የገነቡት ነገሥታት ታሪክ ለዛሬ ስንቅ ኾኖ ድምቀቱ ቀጥሏል፡፡
የድል እንጂ የነጻነት በዓልን አክብራ የማታውቀው ኢትዮጵያ ከቅራት ጠባቂ እስከ ሚሊሻ፤ ከአርበኛ እስከ ወታደር የሙሉ ጊዜ ሥራዎቻቸው ሀገራቸውን መጠበቅ እንደነበር ይነገራል፡፡ ጥንታዊውን የኢትዮጵያን ወታደር ወደ ዘመናዊ የውትድርና ቁመና በመለወጥ እና የዳግማዊ ቴዎድሮስን ምኞት እውን ያደረጉት ታላቁ የጥቁሮች ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ እንደነበሩ ታሪክ ይነግረናል፡፡
ከሀገሩ አልፎ ከኮሪያ እስከ ሊቢያ ፣ ከሶማሊያ እስከ ላይቤሪያ፣ ከሱዳን እስከ ኩባ በዓለም የነጻነት ታሪክ ውስጥ ደማቅ አሻራ የነበረው የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከጀግንነቱ በላይ ታማኝነቱ በርካቶቹን ያስደመመ አኩሪ ታሪክ ነው፡፡
አጼ ምኒልክ የገነቡት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ስሙም ግብሩም ኢትዮጵያን ይመስላል ይባልለታል፡፡
የኢትዮጵያ ወታደር “በተፈተነ ጊዜ ሁሉ የሚፀና የድል ሠራዊት” ነው ሲባል መነሻዎቹ ከሠራዊቱ የየዘመናት የውስጥ ፈተናዎች ባለፈ የሀገሪቷን ፈተናዎች ሁሉ ተሸክሞ ሀገር ያጸና ወታደር በመኾኑ ነው፡፡ ከትናንት እስከ ዛሬ ከውስጥም ከውጪም ፈተና ለማያጣት ኢትዮጵያ ሀገራዊ ዋስትና ሠራዊቷ እንደኾነ ዘልቋል፡፡
በታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!