
ደሴ: ጥቅምት 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ዓላማ ያለው ሰው ፈተና አያስፈራውም፣ ዳገት አያደክመውም፣ ቆልቁለት አያሰለቸውም፣ እሾህና አሜካላው ከእርምጃው አያስቆመውም፣ ሐሩርና ውርጩ ከመጓዝ አያስቀረውም፣ ዓላማ ያለው ሰው ፈተናዎችን እያለፋቸው፣ በፈተናዎቹ ራሱን እያየባቸው፣ ለነገ ሥንቅ እየቋጠረባቸው፣ ትናንትን እያስታወሰባቸው ጉዞውን ይቀጥላል።
ብርቱ ሰው ለዓላማው መስዋዕትነትን ይከፍላል፣ ፈተናዎች እየተደራረቡበት፣ ችግሮች እየበረቱበት፣ ድካም እየበዛበት ወደ ዓላማው ይጓዛል። ፈተናዎችን እያለፈ ወደ ዓላማው ይጠጋል።
ዓላማ ሲኖር ሕይወት ትርጉም ይኖራታል። ለዓላማ የሚከፈል ዋጋ ያበረታል፣ ብልሆች በፈተናዎች ይማራሉ፣ በፈተናዎች አቅማቸውን አሳይተው ይልቃሉ፣ እንደ ወርቅ ተፈትነው ይነጥራሉ፣ ብዙዎችን በሚያስቀረው ማዕበል ሳይደናቀፉ ወደ ከፍታው ይገሰግሳሉ።
ብርቱ ማለት ብዙዎች በደከሙበት፣ ደክመውም በቀሩበት፣ ዓላማቸውንም ባልፈጸሙበት ጎዳና በትጋት የሚዘልቅ፣ ከሁሉም የሚልቅ ነው። ብርቱ ሰው ከብዙዎች መካከል ይገኛል፣ ከሺዎች መካከል ነጥሮ ይወጣል።
መቼም በዚህ ሰሞን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የመነጋገሪያ ርእስ ጉዳይ ኾኖ ሰንብቷል። ከትምህርት ሚኒስቴር የወጣው የተማሪዎች ውጤት ብዙዎችን አነጋግሯል። ብዙዎችንም አስደንግጧል። ጥቂቶችን ደግሞ ጮቤ አስረግጧል።
እንደ አለፉት ዓመታት ሁሉ ብዙ ተማሪዎች አላለፉም። ያለፉት አንሰው ያላለፉት በርክተዋል። የሚያለቅሱት ይበልጣሉ፣ የሚደሰቱት በእጅጉ ያንሳሉ። እናቶች እንደወትሮው ሁሉ በስፋት የልጆቻቸውን ውጤት እያዩ ደስታ አይለዋወጡም፣ ይልቅስ የዓመታት ድካማቸውን እያስታወሱ ይተክዛሉ፣ ድካም መና እያሉ ያዝናሉ እንጂ። ልጆችም ደስ አይሰኙም። ከጓደኞቻቸው ጋር የውጤት መምጣትን ብሥራት አያበስሩም።
ብዙዎች ከበር ወዲህ በቀሩበት፣ ብዙዎች ባዘኑበት፣ ብዙዎችም በደነገጡበት በዚህ ዘመን ድንቅነታቸውን ያስመሰከሩ፣ ከፈተና በላይ የኾኑ፣ ፈተናን ጥለው ያለፉ ጀግና ተማሪዎችም አሉ።
ተማሪ ኤሊያስ ደሳለኝ ይባላል። ተወልዶ ያደገው በታሪካዊቷ ከተማ ደብረ ታቦር ነው። ተወልዶ ባደገባት ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ተከታትሏል። ኤሊያስ ታታሪ እና ነገን ለማሳመር የሚጥር ተማሪ ነው። በትምህርቱ ብርቱና ታታሪ ነው። ታታሪነቱ ደግሞ በውጤት ካሰው።
የ8ኛ ክፍል ፈተናን በተፈተነ ጊዜ ከፍተኛውን ውጤት አስመዘገበ። ይህ ከፍተኛ ውጤትም በተሻለ ትምህርት ቤት እንዲማር እድል ፈጠረለት። ደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤትን ተቀላቀለ።
ኤሊያስ ስለ ትምህርት ሂደቱ ሲናገር “ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ እስከ ስምንተኛ ክፍል በደብረ ታቦር ትምህርቴን ወስጄያለሁ። ስምንተኛ ክፍል ፈተና እንደ ክልል ከፍተኛ ውጤት ነበረኝ። በእርሱ አማካኝነት ለደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት መግቢያ ፈተና ብቁ ኾንኩ። ፈተናውን በመውሰድም ወደ አዳሪ ትምህርት ቤት ገባሁ” ነው ያለኝ።
ከደብረ ታቦር ደሴ ሄዶ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ለመማር ለኤሊያስ እና ለወላጆቹ ፈታኝ ነበር። ነገር ግን ኤሊያስ የተሻለ ትምህርት ለመማር ያለው ጉጉት በለጠበት። “አዳሪ ትምህርት ቤቱን ለማየት ጓጓሁ፣ መሄድ እፈልጋለሁ በሚል ቤተሰብን አስጨንቅ ነበር። እነርሱ ደግሞ እንዴት ብቻውን ይሄዳል የሚል ጭንቀት ላይ ነበሩ። በመጨረሻም እኔም ቤተሰቦቼም ትምህርት ቤቱን ጎበኘነው፣ ነገሮችን ካዩ በኋላ ትምህርት ቤቱ ፍሬ የሚገኝበት ነው ብለው ስላሰቡ በዛው እንድማር ወስነዋል” ብሎናል ያንን ጊዜ ሲያስታውስ።
ለመጀመሪያ ጊዜ ከቤተሰብ ተለይቶ ሲሄድ ከብዶት እንደነበርም ነግሮናል። ናፍቆቱን ችሎ በደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤትም ትምህርቱን ተከታተለ። የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናንም ወሰደ። ኤሊያስ 646 በማምጣት በአማራ ክልል ከፍተኛውን ውጤት አስመዘገበ። በኢትዮጵያ ደግሞ ሁለተኛውን ከፍተኛ ውጤት አመጣ።
ኤሊያስ ስላስመዘገበው ውጤት ሲነግረን “ከፍተኛ ውጤት በማምጣቴ ደስተኛ ነበርኩ ይሄን አልዋሽም፣ ነገር ግን የጠበኩት አይደለም የመጣልኝ። ከፍተኛ ስለኾነ ደስተኛ ኾንኩ እንጂ የጠበኩትና ሠርቼ ይመጣልኛል ብዬ ያሰብኩት እንደዚህ አልነበረም” ነው ያለው።
ኤሊያስ ከነበረው ዝግጁነት፣ እውቀት እና ብርታት አንፃር ውጤቱ ከዚያም በላይ ይኾናል ብሎ ጠብቆ ነበር። በደንብ ሠርቻለሁ ብዬ አስቤ ነበርም ብሎናል።
የደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ ከፍተኛው ውጤት የተመዘገበበት ትምህርት ቤት ነው። ይህ ብቻ አይደለም ሁሉንም ተማሪዎች አሳልፏል። ዘንድሮ ሁሉንም ተማሪዎችን አሳልፏል። በክልሉም ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበበት ትምህርት ቤት ነው። እንደ ሀገር ደግሞ ሁለተኛው ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቦበታል።
ኤሊያስ ከፍተኛ ውጤት እንዲያመጣ መምህራን እና ወላጆች የነበራቸው እገዛ ትልቁን ቦታ ይወስዳሉ ብሏል። ለእነርሱ ሁልጊዜም ትልቅ ምሥጋና አለኝ ነው ያለው። መምህራን ምንም ሳይሳሱ ዋጋ እንደሚከፍሉላቸውም ነግሮናል። ትምህርት ቤቱም ማድረግ የሚችለውን ሁሉ አድርጎልናል ነው ያለው። ለትምህርት ቤቱ ከዚህ በላይ ድጋፍ ቢደረግለት ከዚህ የተሻለ ውጤት ይኖረዋልም ብሏል ኤሊያስ።
ከቤተሰቤ ጋር የተቀራረበ ግንኙነት አለኝ የሚለው ኤሊያስ ወላጆቼን በነፃነት እቀርባቸዋለሁ፣ በነፃነት አማክራቸዋለሁ፤ እነርሱም ሁልጊዜም መፍትሔ ይሰጡኛል ነው ያለን። ወላጆቹ የጤና ባላሙያዎች መኾናቸውን የነገረን ተማሪ ኤሊያስ የትምህርትን ዋጋ በሚገባ የተረዱ በመኾናቸው ለእኔ ልዩ እገዛ ያደርጉልኛል ብሎናል።
“ውጤቴ በዚህ ዓመት ከመጣው ውጤት አንፃር ጥሩ ውጤት ነው፣ በጣምም ተደስቸበታለሁ” ነው ያለን። ኤሊያስ ወደ ፊት እንደ ፈጣሪ ፈቃድ ጄነቲክ ኢንጂነሪንግ የመማር ሕልም አለኝም ብሏል። ዓላማዬን ለማሳካት ወደ ውጭ መሄድና መማር ይኖርብኛል ብሏል።
ኢትዮጵያ ሰላም ኾና ሁሉም በአንድነት ሠርቶ የሚለወጥባት ሀገር እንድትኾን ምኞቴ ነው ያለው ተማሪ ኤሊያስ ለሀገሬ የአቅሜን ማድረግ እፈልጋለሁ፤ ሀገሬ ትደርሳለች ብዬ ከማስባት ቦታ እንድትደርስ የሚጠበቅብኝን ለማድረግ በትምህርቴ እበረታለሁም ብሏል።
ለፈተና የተዘጋጀሁት የራሴን ግብ፣ ለራሴ ነግሬ፣ ራሴን ከራሴ ጋር አነፃፅሬ ነውም ብሎናል። ኤሊያስ ከእርሱ ተከትለው ለሚፈተኑ ተማሪዎች መልእክት ሲያስተላልፍ “በሕይወታቸው አንድ ጊዜ ብቻ ነው የ12ኛ ክፍል ፈተናን የሚወስዱት፣ ይሄን አምነው አንድ ዓመት መስዋዕት ማድረግና ለፈተናው መዘጋጀት አይከብድም። ራስን ማሳመን ብቻ ነው ምስጢሩ፤ ትምህርት ሚኒስቴር ዓላማና ግብ ይዞ ከ700 ይፈትናል። ተማሪዎቹ 700 ያመጡልኛል ብሎም ያስባል። ስለዚህ መውደቅና ማለፍ የሚሉትን ወደ ጎን ትተን 700 ለማምጣት መሥራት አለብን።
አንዳንድ ሰው እንዴት በ12ኛ ክፍል ብቻ መለወጥ ይቻላል ብሎ ያስባል። አንድ ዓመት ራስን ለመለወጥ ከበቂ በላይ ነው። አንድ ቀን አንድ ሳምንት እየተደራረቡ ነው የራስን ለውጥ ማየት የሚቻለው። ከዛሬ ጀምረው መሥራትና መትጋት ከቻሉ ከፍተኛ ውጤት የማይመዘገብበት ምክንያት የለም” ብሏል።
ኤሊያስ ብዙ ሰዓት ወስዶ እንደማያነብ፤ ሲያነብ ግን በደንብ ገብቶት መነሳትን እንደሚወድም ነግሮናል። “የማነበው የማንበብ ፍላጎቴ ሲመጣ ነው። በእርግጥ አንዳንድ ጊዜ ፍላጎት ሲመጣ ብቻ ማንበብ ጥሩ ላይኾን ይችላል። ፍላጎትን መግራት አንዱ ጥበብ ነው። ፍላጎቴ ሲመጣ ነው ቁጭ ብዬ የማነበው። ለማንበብ በምቀመጥበት ሰዓት እውቀት ይዤ መነሳት ላይ እንጂ ክፍለ ትምህርቱን መሸፈን ላይ ትኩረት አላደርግም። ከማነበው ላይ ምን ፍሬ ነገር አገኘሁ ከሚለው ላይ አተኩራለሁ። ፍሬ ነገር ይዤ ስነሳ ያ ጊዜ ለእኔ ስኬት ነው ብዬ እወስዳለሁ” ነው ያለው።
እቅድ ይዞ እቅድን መተግበር ውጤታማ እንደሚያደርግም ገልጿል። “እውነተኛና ብርቱ ሰው ባሕር ላይ ቢጣልም ይወጣል፣ የነገሮች መለዋወጥ፣ የመፈተኛ ቦታ መለዋወጥ ጫና የሚያሳድርብን ከኾነ ራሳችንን ብቁ አይለንም ብለን ራሳችንን መመዘን ያስፈልጋል” ብሏል።
በራስ መተማመንን ማሳደግ እንደሚገባም ገልጿል። የአፈታተን ሥርዓቱ ከተለመደው እየተለየ ሊሄድ እንደሚችል ያነሳው ተማሪ ኤሊያስ ለዛ ዝግጁ መኾን እንደሚገባም ተናግሯል። መምህራን ለተሻለ ውጤት አበርክቷቸው ከፍ ያለ ነውም ብሏል።
ተማሪ ኤሊያስ የትኛውንም ማኅበራዊ ሚዲያ እንደማይጠቀምም ነግሮናል። ማኅበራዊ ሚዲያን አለመጠቀሜ ለውጤቱ ማማር አግዞኛልም ብሎናል። አስፈላጊ በኾነ ጊዜ ማኅበራዊ ሚዲያ ይኖረኛል ነው ያለው። በራሴ አቋም መፅናት፣ በራሴ መንገድ መጓዝ ያስደስተኛል ያለው ተማሪ ኤሊያስ ማኅበራዊ ሚዲያ ጫና አላሳደረብኝም ብሏል።
በሚቀጥሉት ጊዜያት የሚፈተኑ ተማሪዎች አስቀድመው መዘጋጀት፣ በራስ መተማመንን ማሳደግ እና ዓላማ ይዘው መነሳት እንደሚገባቸውም መክሯል። ዓላማ ካለህ ፈተና አያስፈራህም ነው ያለው።
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!