
ባሕር ዳር: ጥቅምት 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ባለፉት ዓመታት በተከሰተው ጦርነት ምክንያት በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የጥገና እና የጥናት ሥራ መሥተጓጎሉን የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ገልጿል።
በዚህ ዓመትም በክልሉ በተከሰተው የሰላም መደፍረስ ጥናት ለማድረግ መቸገሩን ባለስልጣኑ ገልጿል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው እንዳሉት የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት መጠለያ ሥራ፣ በዘላቂነት ለመጠበቅ፣ ለመንከባከብ እና አስቸኳይ ጥገና የሚያስፈልጋቸውን ደግሞ በዘላቂ ላሊበላ ፕሮጀክት ለመሥራት ትኩረት ተደርጎ ወደ ሥራ ተገብቷል።
ባለፈው ዓመት እንደ ድልድይ፣ የመጓጓዣ መንገዶች፣ የብራና ቅርሶችን “ዲጅታላይዝድ” የማድረግ፣ የማፋሰሻ ሥራ፣ የቤተ ክርስቲያኑን ውስጥ ማስተካከል፣ የኤሌክትሪክ ኢንስታሌሽን፣ የዲዛይን ማስተካከያ ሥራ፣ ዓለት ላይ እንዴት ጥገና ማድረግ እንደሚቻል ለአካባቢው ነዋሪዎች ሥልጠና መሥጠት የመሳሰሉ ሥራዎች በዘላቂ ላሊበላ ፕሮጀክት ሲከናወኑ ቆይተዋል።
ይሁን እንጅ በአካባቢው በተከሰተው የጸጥታው ችግር ፕሮጀክቱ መቋረጡን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
ሌላኛው ከዚህ በፊት የተሰሩትን የአብያተ ክርስቲያናቱን መጠለያዎች ማንሳትና በሌላ መጠለያ መተካት ከሚከናወኑት ተግባራት አንደኛው እና ዋነኛው ፕሮጀክት ነው ተብሏል።
የነበሩ መጠለያዎችን አንስቶ በሌላ ለመተካት ከአብያተ ክርስቲያናቱ ውጭ ያለውን ዋናው ዓለት መጠለያዎቹን መያዝና አለመያዙን የሚያረጋግጥ፣ የጉድጓድ ናሙና፣ የመጠለያው የውኃ ተፋሰስ እና መጠለያውን በከባድ ብረት ከመሥራት ይልቅ ቀርቃሃን በመቀቀልና በማጠንከር መሥራት ቢቻል ምን ያህል ተስማሚ እና አዋጭ እንደሚኾን የሚያሳዩ ጥናቶች እንደገና ተጠንተው እንዲቀርቡ ዩኔስኮ ጠይቋል።
ይሁን እንጅ ባለፉት ዓመታት በነበረው ጦርነት ምክንያት ጥናቱን ማካሄድ አለመቻሉን ነው ዋና ዳይሬክተሩ የገለጹት።
አሁን ላይ ጥናቱን ለማካሄድ ጨረታ መውጣቱን የገለጹት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው የአካባቢው ሰላም ካልተመለሰ አሁንም ጨረታው ሊዘገይ እንደሚችል ገልጸዋል። በዚህ ዓመት ሰላሙ ወደ ነበረበት ከተመለሰ ደግሞ ጥናቱ እንደሚከናወን ተገልጿል።
ያለፈው ትውል ደኅንነቱን አስጠብቆ ያስተላለፈውን ቅርስ የአሁኑ ትውልድ ደግሞ ቅርሶችን መጠበቀና መንከባከብ ለቀጣይ ትውልድ የማሻገር ግዴታውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት መረጃ እንደሚያሳየው ላሊበላን ለመጠገን የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች በ2014 ዓ.ም መጨረሻ ነበር ወደ ሥራ የገቡት።
ፕሮጀክቶቹ የሶስት ዓመት ተኩል መርሃ ግብር መኾናቸው ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!