
ባሕር ዳር: ጥቅምት 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ እና መካከለኛ የሥራ ኀላፊዎች በወቅታዊ የሰላም ጉዳዮች ዙሪያ በጎንደር ከተማ የግምገማ መድረክ እያካሄዱ ነው። በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ ክልሉ የገጠመውን የሰላም እጦት ችግር በውይይትና በመግባባት መፍታት ይገባል ብለዋል። በአማራ ክልል አዳዲስ አመራሮችን የማዋቀር ሥራ ሲከናወን መቆየቱንም ጠቅሰዋል። የአዳዲስ አመራሮችን አቅም የመገንባት ሥራም እየተከናወነ ነው ብለዋል።
አቶ ይርጋ በክልሉ ያጋጠመው አለመረጋጋት በልማት ሥራዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩንም ተናግረዋል። “በየደረጃው የሚገኙ የክልሉ የሥራ ኀላፊዎች ለሰላም መረጋገጥ፣ ለሕግ የበላይነት መከበርና ለልማት በቁርጠኝነት ሊሠሩ ይገባል” ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።
“ሕዝብ የሚያነሳቸው በርካታ የልማትና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች አሉ” ያሉት አቶ ይርጋ አመራሩ ሕዝቡን በማደራጀት እና ተደማምጦ በመሥራት ጥያቄዎች መፍትሔ እንዲያገኙ ይሠራል ብለዋል።
በመድረኩ የተሳተፉ የሥራ ኀላፊዎችም የክልሉን ሰላም በዘላቂነት ለመመለስና የልማት ሥራዎችን ለማፋጠን ጠንክረው እንደሚሠሩ አስታውቀዋል።
ዘጋቢ:- አገኘሁ አበባው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!