
አዲስ አበባ: ጥቅምት 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአህጉሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት እና ማኅበራዊ ለውጥ በተለይም በገበያ ትስስር ፣ በልምድ ልውውጥ ፣ በቅንጅታዊ አሠራር ትልቅ አቅም የሚፈጥረው የዓለምአቀፍ የስታርታፕ ሽልማት በሳይንስ ሙዚዬም መካሄድ ጀምሯል፡፡
ዝግጅቱ በግሎባል ኢኖቬሽን ኢኒሼቲቭ ግሩፕ የተዘጋጀ ነው፡፡ ዝግጅቱ ልዩ የፈጠራ አቅም ያላቸውን በማወዳደር ለአሸናፊዎቹ ማበረታቻ እና ዕውቅና የሚሰጥበት ነው።
ከመላው አፍሪካ በመጡ ስታርትአፕ መካከል ትብብርና የዕውቀት ልውውጥ የሚደረግበት እንዲሁም በኢትዮጵያ የመስኩ ተዋንያን ትልቅ እድልም የሚያገኙበት እንደኾነ ነው የተገለጸው፡፡ ቅንጅታዊ አሠራርን ለዓለም ማሳየት የሚቻልበት መድረክ ይኾናልም ተብሏል።
በሀገር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ስታርትአፕ ሥነ-ምሕዳሮች መካከል ያለውን ግንኙነት በማፋጠን በአፍሪካ ፈጠራን መሰረት ያደረገ ኢኮኖሚ እንዲገነባ ያግዛል። አቅሞችንና ሀብቶችን አቀናጅቶ በመሥራት ውጤታማነትን ለማሳደግ እንዲሁም የተቀናጀ አሠራርን ባሕል ለማድረግ የሚያስችል ልምድ እንደሚገኝበት ይጠበቃል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ.ር) የወጣቶችን የሥራ ፈጠራ አቅም በመጠቀምና በመደገፍ የሥራ ፈጠራ እና የስታርት አፕ ምሕዳሩን በማስፋት ጠንካራና ዘላቂ ኢኮኖሚ መገንባት ይቻላል ብለዋል፡፡ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያም ለዘርፉ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች መኾኑን ገልጸዋል።
ይህ ታላቅ ዓለማቀፍ መድረክም አቅሞችን አስተባብሮ የሚሠራበትን ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው ኢትዮጵያ ታላቅ ታሪክ ፣ ሰው ሠራሽና ተፈጥሮአዊ ቅርሶች ያሏት ሀገር ናት ፤ ይህም ምን ያህል የፈጠራና መሰል አቅሞች ባለቤት መኾኗን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአህጉሩ ያላትን ተፅዕኖ ተጠቅማ ወጣቶቿን ለፈጠራ ታነሳሳለች ፤ የሥራ ፈጣሪዎቿን አቅም ታሳድጋለች ፤ ድንበርየለሸ አህጉራዊ አስተዋጽኦ ታደርጋለች ሲሉም ተናግረዋል። የማይበገር ኢኮኖሚን ለመገንባትም ትጥራለች ነው ያሉት፡፡
ሚኒስትሯ በትብብር መንፈስ ከአህጉሩና ከዓለም ጋር ለመወዳደር እንዲሁም ለመገናኘት አቅምን አስተባብሮ በመሥራት የወጣቶችን የፈጠራ ውጤቶች ለመጠቀም እንደሚሠራም አስገንዝበዋል። የሥራ ፈጠራና የስታርትአፕ ምህዳሩን ለማስፋት በጋራ አብረን እንቁም የሚል መልዕክታቸውንም አስተላልፈዋል።
የግሎባል ስታርትአፕ አዋርድ መስራች ኪም ባሊ እዚህ የተገኛችሁ የአፍሪካን አቅም ይዛችሁ ነውና እኛም አፍሪካ ያላትን አቅም እናደንቃለን ወደ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመለወጥም አጋርነታችንን እናረጋግጣለን ብለዋል። አፍሪካ ብዙ ሥራ ፈጣሪዎች አሏት ፤ ብዙ ሥራ ፈጣሪዎችንም ትፈልጋለች ነው ያሉት።
የአፍሪካን ብሎም ኢትዮጵያዊያን ወጣት ሥራ ፈጣሪዎችን ለመደገፍ መሥራት አለብን ብለዋል የአፍሪካ ስታርት ታፕ አዋርድ ኀላፊዋ ጆ ግሪፍዝ፡፡
ኀላፊዋ ለዚህም አብረን በጋራ እንሠራለን ምክንያቱም ብዙ አቅም እና ባለ ብሩህ አእምሮ ወጣቶች ያሉባት አህጉር ስለኾነች ነው ያሉት፡፡
በዝግጅቱ ከ8 ሺህ 277 ተወዳዳሪዎች 71 አህጉራዊ አሸናፊዎችና 15 የአሸናፊዎች አሸናፊዎች ዕውቅናና ሽልማት ይደረግላቸዋል።
ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግሥቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!