
ባሕር ዳር: ጥቅምት 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የኤች አይቪ ስርጭትን ለመከላከል ዘርፈ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ ነው፡፡ ከእነዚህ ጥረቶች መካከል በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ያሉ ሠራተኞች ራሳቸውን እንዲጠብቁ እና ሌላውንም ለመጠበቅ የሚያስችላቸውን ዕውቀት እንዲያገኙ ሰፊ ትምህርት እንዲሰጥ ታሳቢ ተደርጎ ተግባራዊ መደረግ ከጀመረ ቆይቷል፡፡
በበሽታው ዙሪያ የመመካከር እና የመወያት ሥራን በበጀት ይደገፍ ዘንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከበጀታቸው ሁለት በመቶ የሚኾነውን ጥቅም ላይ እንዲያውሉ ለማድረግ ታሳቢ ያደረገ አሠራርም ተግባራዊ አድርጎ ሲሠራ ነው የቆየው፡፡
ለመኾኑ ይህ አሠራር ምን ያክል ውጤታማ ኾኗል? ምን ያህል ተግባራዊ እየኾነ ነው? ሲል አሚኮ አሠራሩን ለመፈተሽ ጥረት አድርጓል፡፡
አሁን ላይ በአማራ ክልል ባለው የሰላም እጦት አብዛኞቹ መሥሪያ ቤቶች ተግባራዊ እያደረጉት ባይኾንም ሰላም በተረጋገጠባቸው አካባቢዎች አሠራሩ እየተተገበረ እንደሚገኝ ለመታዘብ ተችሏል፡፡
አሠራሩን እና የተገኘውን ውጤት በተመለከተ በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠር ዘርፈ ብዙ ምላሽ ዳይሬክተር ውድነህ ገረመው በአማራ ክልል ኤች አይቪ ኤድስን ለመከላከል ሰፊ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ነግረውናል፡፡
በተለይም ለበሽታው አጋላጭ የሥራ ኹኔታ ያላቸውን ሠራተኞች ለመጠበቅ በሚል የተተገበረው አሠራር ሰላሙ በተረጋገጠበት ጊዜ ውጤታማ እንደነበር ነው ያስገነዘቡት፡፡
ቢሮው በዚህ ዓመት በመሥሪያ ቤቶች 15 ሚሊዮን 310 ሺህ ብር በጀት ለማስመደብ አቅዶ ሲሠራ ቢቆይም በክልሉ ባጋጠመው የሰላም እጦት 6 ሚሊዮን 419 ሺህ ብር ብቻ ማሰባሰብ እንደተቻለ ነግረውናል፡፡
በሽታውን ለመከላከል በተካሄደው ውይይትም በሩብ ዓመቱ 535 ሺህ 718 ብር መጠቀም እንደተቻለ ነው ያብራሩት፡፡
አቶ ውድነህ እንደነገሩን ቢሮው በበሽታው ምክንያት ጉዳት ለሚደርስባቸው ድጋፍ የሚውል 6 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ እንደቻለም አብራርተዋል፡፡
እስካሁንም በሽታው ባመጣው ችግር ለጉዳት የተዳረጉ ሕጻናት ድጋፍ እንዲያገኙ ተደርጓል ነው ያሉት። ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው ዜጎች ድጋፍ እንዲያገኙ መደረጉንም አረጋግጠዋል፡፡
ዳይሬክተሩ ኤች አይቪ ኤድስ መረጋጋት በሌለባቸው አካባቢዎች የመስፋፋት እድሎች እና ለበሽታው የሚያጋልጡ ምክንያቶች ይበልጥ እንደሚሰፉ ገልጸው በዚህ ወቅት ከምንጊዜውም በላይ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!