
ባሕር ዳር: ጥቅምት 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ እና መካከለኛ የሥራ ኀላፊዎች የክልሉን ወቅታዊ ኹኔታዎች እየገመገሙ ነው። በአብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች የሰላም ኹኔታ እየተሻሻለ ስለመምጣቱ ተገልጿል።
በመድረኩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ለቀናት ሲሰጥ የቆየው የብልጽግና ፓርቲ ሥልጠና በየደረጃው ያሉ የክልሉ የሥራ ኀላፊዎች ለክልሉ ሰላም እና ሁለንተናዊ ልማት የበለጠ እንዲተጉ የሚያስችል ስለመኾኑ አንስተዋል።
አመራሮች በቀጣይነት ወደ ሥራ ሲገቡ የተጀመሩ የሕዝብን ሰላም የማስጠበቅ ሥራዎችን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።
“የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ እና ዘላቂ ሰላም ማስፈን ተቀዳሚ ተግባራችን ነው” ሲሉ ነው ርእሰ መሥተዳድሩ የተናገሩት።
የሰላም እና የልማት ሥራችንን የሚያፋጥን ምቹ ኹኔታ የመፍጠር ሥራም አንዱ የክልሉ ትኩረት ስለመኾኑም ርእሰ መሥተዳድሩ ተናግረዋል።
“ክልሉ ለሕዝብ ልማት እና ሰላም የሚሠሩ ብቁ አመራሮችን ይፈልጋል” ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ በክልል እና በዞን ደረጃ የአመራር ምደባ መደረጉን ጠቁመዋል።
በቀጣይም በወረዳ እና በቀበሌ ደረጃ አመራሮችን የመመደብ ሥራ በትኩረት ይከናወናል ነው ያሉት። የተመደቡ አመራሮችም በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማስቻል ሰፊ ርብርብ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
በክልሉ ቀልጣፋ የመልካም አሥተዳደር እና የመንግሥት አገልግሎት ተደራሽ እንዲኾን በጥብቅ ክትትል የሚመራ ተግባር እንደሚከናወንም ርእሰ መሥተዳድሩ ገልጸዋል።
በተለይም ሰላማቸው በተረጋገጡ የክልሉ አካባቢዎች ምቹ የአገልግሎት አሰጣጥ ተዘርግቶ የተጀመሩ ልማቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ይሠራል ብለዋል።
ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በድርቅ ምክንያት ጉዳት እየደረሰ ስለመኾኑ ጠቁመዋል። ለችግር የተጋለጡ ወገኖች ከአስቸኳይ የዕለት ደራሽ እርዳታ ጀምሮ እስከ ዘላቂ ማቋቋሚያ የሚኾን እርዳታ እንዲያገኙ በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል።
የድርቅ ተጎጂዎችን ለመደገፍ ከመንግሥት በተጨማሪ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባም ርእሰ መሥተዳድሩ መልእክት አስተላልፈዋል።
መድረኩ ላይ የክልሉ አሁናዊ የሰላም ሁኔታ በጥልቀት ተገምግሞ ቀጣይ አቅጣጫዎችም ይቀመጣሉ ተብሏል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!