
ባሕር ዳር: ጥቅምት 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የፕሪምየር ሊጉ አራተኛ ሳምንት ዛሬ ቀን 9 ሰዓት ላይ ሻሸመኔ ከተማ ከሲዳማ ቡና ፤ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሚያደርጉት ሁለት ጨዋታዎች ይጀመራል፡፡
ቀን 9 ሰዓት ላይ በፕሪሚየር ሊጉ ሦስት ሽንፈቶችን አስተናግዶ ምንም ነጥብ ማስመዝገብ ያልቻለው ሻሸመኔ ከተማ ሲዳማ ቡናን ይገጥማል። የሻሸመኔ ቡድን ያደረጋቸውን ጨዋታዎች ቢሸነፍም ያጨዋወት ዘይቤው ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ በጥሩ የመሻሻል ሂደት ላይ መኾኑን አሳይቷል፡፡ ፋሲል ከነማን በገጠመበት ጨዋታ የነበረው እንቅስቃሴ ለቡድኑ መሻሻል አብነት ነው ምንም እንኳን ቢሸነፍም፡፡
ሲዳማ ቡናዎችም ልክ እንደ ተጋጣሚያቸው ሁሉ ጥሩ አጀማመር አላደረጉም። ከሦስት ጨዋታዎች ያስመዘገቡት ነጥብ አንድ ብቻ ነው። ስለኾነም በዛሬው ጨዋታ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድል ለማግኘት አልመው ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በጨዋታው ሲዳማ ቡና ተጭኖ የሚጫወት ቢኾንም ሻሸመኔ ከተማም በቀላሉ የሚረታ አይደለም፡፡
ምሽት 12 ሰዓት ላይ ደግሞ ድሬዳዋ ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው፡፡
ድሬዳዋ ከተማ ከሦስት ጨዋታዎች አራት ነጥብ በመያዝ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ በ11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ቡድኑ ያደረጋቸውን ጨዋታዎች በመሸነፍ ፣ በማሸነፍ እና በአቻ ማጠናቀቁ የቡድኑን አቋም ወጥ አለመኾን ያሳየ ነው፡፡
ቡድኑ ባደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች ኳስ በመቆጣጠር ፣ በመስመር በማጥቃት እና በረዣዥም ኳሶች የግብ ዕድሎች ለመፍጠር የሚያደርገው ጥረት ግሩም ነበር፡፡ የኾነ ኾኖ ድሬዳዋ ዛሬ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ያለውን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን እንደ መግጠሙ በትኩረት መጫወት ግድ ይለዋል፡፡
በአምስት ነጥብ በ7ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እስካሁን ባካሄደው ጨዋታ ሁለት ግቦች አስቆጥሮ አንድ ግብ ብቻ ነው የተቆጠረበት፡፡ ይህም የቡድኑን ጠንካራ የመከላከል ብቃት የሚያሳይ ነው።
አጥቂዎችም በየጨዋታው በርካታ የግብ ዕድሎች ሲፈጥሩ መታየታቸው ድሬዳዋ ከተማ ሊያሸንፍበት የሚያስችለው ምክንያት ነው፡፡
እንደ ሶከር ኢትዮጵያ ዘገባ ፤ ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 12 ጊዜ ተገናኝተው ድሬዳዋ አምስቱን በማሽነፍ ቀዳሚ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክም አራቱን በድል ተወጥቷል። ሦስቱ ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቅቀዋል። 21 ግቦች በተቆጠሩበት የእርስ በርስ ግንኙነት ታሪክ አንድ ጊዜ ብቻ ግብ ሳይቆጠር የተጠናቀቀ ሲኾን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 11፣ ድሬ ዳዋ ከተማ 10 ግቦችን አስቆጥረዋል።
ፕሪሚየር ሊጉ በእለተ ሐሙስ ጥቅምት 15 ቀን 2016 ሲቀጥል ቀን 9 ሰዓት ሐዋሳ ከተማ ከኢትዮጵያ መድን ይገናኛሉ፡፡ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ደግሞ ወልቂጤ ከተማ ከባሕር ዳር ከተማ የሚጫወቱ ይኾናል፡፡
ዘጋቢ፡- ሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!