የአፍሪካ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች በወታደራዊ መስኩ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ትሥሥር ለማሳደግ እንደሚሠሩ ገለጹ።

43

ባሕርዳር፡ ጥቅምት 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ረጅም ዘመናት የካበተ የሠራዊት ግንባታ ያላት በመኾኑ ከሀገሪቱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ እንደሚሠሩ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች ገለጹ።

116ኛውን የመከላከያ ሠራዊት ቀንን አስመልክቶ የሠራዊቱን ታሪክ፣ ተጋድሎና አሁን የደረሰበትን አስተማማኝ ቁመና የሚያሳይ የፎቶ አውደ ርዕይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ለሕዝባዊ እይታ ቀርቧል።

በመከላከያ ሚኒስቴር የወታደራዊ ታሪክ ቅርስ ጥናትና አሥተዳደር ዳይሬክቶሬት ተወካይ ኃላፊ ሌተናል ኮሎኔል አግዘው አልታየ አውደ ርዕዩ የሠራዊቱን የጀግንነት ታሪክና አኹን የደረሰበትን አስተማማኝ ቁመና የሚያመላክት ነው ብለዋል።

ሠራዊቱ ለኢትዮጵያ ሉአላዊነት የከፈለውን ዋጋ እና ታሪካዊ ጀግንነቱን መዘከርም የአውደ ርእዩ ዋና አለማ ነው ሲሉ አብራርተዋል።

የተዘጋጀውን አውደ ርእይ ለመታደም የመጡት የአፍሪካ ሀገራት ሚሊተሪ አታሼዎች አውደ ርእዩ የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት ታሪክ በጥልቀት እንድንረዳ ያስቻለን ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያና በአፍሪካ ኅብረት የዚምባቡዌ ሚሊተሪ አታሼ ብርጋዴር ጄኔራል ኢኔስ አሻሙ አውደ ርእዩ ስለ ኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ታሪክ የነበራቸውን ግንዛቤ የሚያሳደግ ኾኖ እንዳገኙት አብራርተዋል።

ኢትዮጵያና ዚምባቡዌ በወታደራዊ መስኩ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው አንስተው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የዘርፉን ግንኙነት የሚያጠናክሩ ሥራዎች በመከናወን ላይ መኾናቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የጋቦን ሚሊተሪ አታሼ ኃላፊ ኮሎኔል አርስቲዴ አንጉሌት በበኩላቸው አውደ ርእዩ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የገዘፈ ታሪክ ባለቤት መኾኑና የሠራዊቱን ሁለገብ እድገት የታየበት ስለ መኾኑ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ያለው እምቅ አቅም ለአፍሪካ ሀገራትም ምሳሌ መኾኑን አውስተው ጋቦን እና ኢትዮጵያ በወታደራዊ ዘርፉ ያላቸውን ትሥሥር ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እንደሚከናወን ተናግረዋል።

ኢዜአ እንደዘገበው 116ኛውን የመከላከያ ሠራዊት ቀን አስመልክቶ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትር የተዘጋጀውን የፎቶ አውደ ርዕይ አርበኞች፣ የቀድሞ የሠራዊት አባላት እና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እየጎበኙት ይገኛል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበድርቅ ለተጎዱ ዜጎች እስካሁን የቀረበው ድጋፍ በቂ ባለመኾኑ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሰሜን ጎንደር ዞን አሥተዳደር ጠየቀ።
Next articleየኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል፡፡