
ባሕር ዳር: ጥቅምት 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ድርቁ ያስከተለው ችግር ሰፊ በመኾኑ ሰዎች አካባቢያቸውን እየለቀቁ መኾናቸውም ተነግሯል።
አርሶ አደር ኀይሉ መንግሥቴ በሰሜን ጎንደር ዞን የጠለምት ወረዳ ነዋሪ ናቸው። በ2015/16 የምርት ዘመን በተከሠተው ድርቅ ምክንያት ሰብል አልበቀለም ፤ ምንጮች ስለደረቁ መስኖ ለመጠቀም አልተቻለም ፤ ”በአይን የሚታይ ነገር ሰብል የለም” ብለዋል።
አስር ቤተሰብ እንዳላቸው የገለጹት አርሶአደር ኀይሉ ችግሩ እየፈተናቸው እንደኾነም ነግረውናል። ችግሩን ለማቃለል እርዳታ ቢጀመርም በልቶ ለማደር የሚበቃ አልኾነም እንደ አርሶ አደሩ ሃሳብ።
በድርቁ ምክንያት እንስሳትም ለረሃብና ለበሽታ ተጋልጠዋል ፤ ”እኔም እንስሳቶች ሞተውብኛል” ነው ያሉት።
በሰሜን ጎንደር ዞን በ3 ወረዳዎች እና 32 ቀበሌዎች የከፋ ድርቅ መከሠቱን የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ ገልጸዋል። በአጠቃላይ 451 ሺህ ሕዝብ ለችግር በመጋለጡ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልገውም ጠቅሰዋል።
እንደዋና አሥተዳዳሪው ድርቁ ያስከተለው ጉዳትን ያባባሱ ምክንያቶች :-
👉 የሰሜኑ ጦርነት በአካባቢው ያደረሰው ተጽዕኖ፣
👉 የ2015/16 የምርት ዘመን የዝናብ እጥረት እና
👉 የሰብል በሽታዎች ናቸው።
በድርቅ የተጎዳው ሕዝብ ወደ ጎረቤት ወረዳዎች የመሰደድ እና ወደ ወረዳ ማዕከል ለመሰብሰብ መፈናቀል ጀምሮ እንደነበር አሥተዳዳሪው ተናግረዋል። በቂ ባይኾንም ድጋፍ በማድረግ ወደ ቀየው እንዲመለስ መደረጉንም ጠቅሰዋል።
”የክልሉ እና የፌዴራል መንግሥት ለችግሩ ለመድረስ እየሞከሩ ነው” ያሉት ዲያቆን ሸጋው መንግሥታዊ ካልኾኑ በጎ አድራጊ ድርጅቶች ጋርም ስለ ችግሩ ውይይት ተደርጎ ምላሽ እየተጠበቀ መኾኑን ገልጸዋል።
ዋና አሥተዳዳሪው እንስሳት ግጦሽ በሚያገኙበት አካባቢ እንዲቆዩ በማድረግ ችግሩን ለማለፍ እየተሞከረ መኾኑን ገልጸው፤ በድርቁ ምክንያትም የእንስሳት በሽታ በመከሰቱ የክልሉ መንግሥት በቂ መድኃኒት ልኳል ብለዋል።
”ከሀገር ውስጥም ከውጪም ድጋፍ እየሰበሰበን ችግሩ ለጠናባቸው ቅድሚያ ሰጥተን ድጋፍ እያደረግን ነው” ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው እስካሁን የቀረበው ድጋፍ በቂ ባለመኾኑ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አድርገዋል።
ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!