
ደብረ ብርሃን: ጥቅምት 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) እንደ ኢትዮጲያ ባሉ የጋራ የአኗኗር ዘይቤን የሚከተሉ ሀገራት ውስጥ በጋራ መሥራት ውጤታማ ያደርጋል። ምርታማነት እንዲያድግ፣ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትም እንዲጎለብት በጋራ የሚከናወኑ እንደ ደቦ ፣ ወንፈል እና የመረዳጃ ዕድሮች በራስ አቅም ችግሮችን የመፍታት ልምድ ማሳያዎች ናቸው።
በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህሩ መለሰ አበበ በአነስተኛ የሥራ መስኮች በጋራ የሚጀመሩ እንቅስቃሴዎች አድገው የትልቅ ሀብት ባለቤት ያደርጋሉ ብለዋል። እያንዳንዱ ሰው የራሱ የኾነ አቅምና ክሕሎት አለው ፤ እሱን በማቀናጀት በጋራ መሥራት ደግሞ የስኬት በርን ይከፍታል ነው ያሉት።
በጋራ ሲሠራ ብዙ ፈታኝ ኹኔታዎች እንዳሉ የሚያነሱት መምህሩ የጋራ ግብ ማስቀመጥ ፣ ፍትሐዊ የሥራ ክፍፍል እንዲኖር ማስቻል እና ለተከናወነው ሥራ ተመጣጣኝ ክፍያ መክፈል ለውጤት እንደሚያበቃ መክረዋል። በጋራ ሥራ ላይ ውሳኔ ሰጭነትን ማዳበር እና ግጭቶች ሲገጥሙ ፈጣን መፍትሔ በማስቀመጥ ወደ ቀጣይ ግብ ማማተር ያስፈልጋል ብለዋል መምህሩ።
ብዙ የሥራ አጥ ቁጥር ባለበት ሀገር በጋራ መሥራት የሥራ ዕድል ከመፍጠር አንጻር የማይተካ ሚና ያለው ስለመኾኑም ገልጸዋል። በጋራ መሥራት በኢኮኖሚ ራስን ለመቻል ፣ ለማኅበረሰቡ አገልግሎት ለመስጠት እና ለሀገር የኢኮኖሚ የራስን አሻራ ለማሳረፍ ሚናው የጎላ እንደኾነም መምህሩ ይናገራሉ። “ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻችንን በዘላቂነት ለመፍታት በጋራ የመሥራት ባሕልን ማዳበር ይገባል” ሲሉም መክረዋል።
ለአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ ነውና ያለንን ገንዘብ ፣ ዕውቀት ፣ ሀሳብ እና ክህሎት በማቀናጀት በሥራ ላይ ማዋል ብሎም ከራስ አልፎ ለሀገር የሚበቃ ሀብት እና ንብረት ማካበት ይቻላል ሲሉም መምህሩ አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- ገንዘብ ታደሰ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!