በአማራ ክልል ግማሽ ሚሊዮን አርሶ አደሮች በቡና ልማት እየተሳተፉ እንደኾነ ተገለጸ።

58

ባሕር ዳር: ጥቅምት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ግማሽ ሚሊዮን አርሶ አደሮች በቡና ልማት እየተሳተፉ እንደኾነ ተገልጿል። በክልሉ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በመሥኖ መልማት የሚችል መሬት እንደሚገኝም የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያሳያል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የአትክልትና ፍራፍሬ ባለሙያ አወቀ ዘላለም በክልሉ ያለውን በመሥኖ የመልማት አቅም በመጠቀም የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን ማልማት እንደሚቻል ተናግረዋል። ባለፉት 20 ዓመታት በክልሉ የቡና ልማት ተግባራዊ እየኾነ እንደኾነም ገልጸዋል። ይሁን እንጂ በተሰጠው ትኩረት ማነስ ምክንያት ባለው የመልማት አቅም ልክ ማስፋት አልተቻለም ነው ያሉት። አሁን ላይ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን በክልሉ የማስፋት ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

በአማራ ክልል በ21 ወረዳዎች በኩታ ገጠም ጭምር ቡና እየተመረተ እንደሚገኝ ባለሙያው ገልጸዋል። ማቻከል፣ ጎዛመን፣ ባሕር ዳር ዙሪያ፣ ሜጫ፣ ቡሬ፣ ፍኖተ ሰላም፣ ደራ እና ማዕከላዊ ጎንደር ደግሞ ቡና ከሚመረትባቸው ወረዳዎች ውስጥ ተጠቃሾች ናቸው።

በየዓመቱ እስከ 3 ሺህ ሄክታር መሬት ተጨማሪ መሬት በክልሉ በቡና እየለማ እንደሚገኝም በባለሙያው ተገልጿል።

እስከ አሁን 38 ሺህ ሄክታር መሬት በቡና እየለማ ይገኛል፤ 28 ሺህ ሄክታሩ ምርት እየሰጠ ነው፤ በዚህም ግማሽ ሚሊዮን የሚኾኑ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ነው።

የቡና ጥራትን ለማስጠበቅ በትክክል እንዲለቀምና በተገቢው እንዲሰጣ ግብርና ቢሮው ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራዎችን እየሠራ ነው። ቡናን በጥራት ከማምረት ባለፈ ማኅበራት እና ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የተመረተውን ቡና በትክክል ተፈልፍሎና ተቀሽሮ ለገበያ እንዲቀርብ የማድረግ ኀላፊነት እንዳለባቸው ገልጸዋል። ግብይቱን ማስተሳሰር፣ የራሱ የኾነ ልዩ ባለሙያ እንዲኖር ማድረግ፣ ጥራት ላለው ችግኝ ትኩረት መሥጠት እና የመሳሰሉ ጉዳዮችም እንደክልል በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባም ባለሙያው ጠቁመዋል።

ለዘርፉ የሚኾን የብድር አቅርቦት ማዘጋጀት፣ ማኅበራትን ማዋቀር እና የራሱ መለያ ስም ወይም ብራንዲንግ ማውጣት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

በአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል የወራሚት አትክልትና ፍራፍሬ ምርምር እና ሥልጠና ንዑስ ማዕከል የቡና ተመራማሪ መለሰ ዋለ የቡና ልማትን በክልሉ ለማስፋት የምርምር ቴክኖሎጅዎችን በማውጣት፣ የወጡ ቴክኖሎጅዎችን እና የመነሻ ዘር ጭምር ወደ አርሶ አደሮች የማድረስ ሥራ እየሠራ ይገኛል ብለዋል። በተለይም ከጅማ ምርምር ማዕከል የተለቀቁ የተለያዩ የቡና ዝርያዎችን ከአካባቢው ሥነ ምሕዳር ጋር የማላመድ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በቅርቡም ምርምር ማዕከሉ ምርታማነታቸው በሄክታር ከ15 ኩንታል እስከ 18 ኩንታል የሚደርስ ሦስት የቡና ዝርያዎችን በባሕር ዳር ዙሪያ፣ ይልማናና ዴንሳ እና ሰሜን ሜጫ ወረዳዎች የቅድመ ማስፋት ሥራ አየሠራ ይገኛል። በምርምር ማዕከሉ የሚወጡ መነሻ ዝርያዎችን ደግሞ ግብርና ቢሮው እያሰፋ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ ለመሰብሰብ ኮምባይነር እንደሚያስፈልጋቸው የሰሜን ሸዋ ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡
Next article“ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻችንን በዘላቂነት ለመፍታት በጋራ የመሥራት ባሕልን ማዳበር ይገባል” የምጣኔ ሀብት መምህር መለሰ አበበ