
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ፣ ሳይበላሹ እና ከብክነት በጸዳ መልኩ ለመሰብሰብ ኮምባይነር እንደሚያስፈልጋቸው የሰሜን ሸዋ ዞን አርሶ አደሮች ተናግረዋል። በአማራ በክልል ትርፍ አምራች ከኾኑ አካባቢዎች ውስጥ ሰሜን ሸዋ ዞን አንዱ ነው፡፡ በዞኑ በምርት ዘመኑ የደረሱ ሰፊ ሽፋን ያላቸው ሰብሎችን ምርት በማይባክን መንገድ ለመሰብሰብ ጥረት እየተደረገ ነው የሚገኘው፡፡
በሰሜን ሽዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር በቀለ አየሁ በተያዘው የምርት ዘመን ከራሳቸው አልፈው ለገበያ የሚበቃ የጤፍ ሰብል እንዳላቸው ነግረውናል። አርሶ አደር በቀለ ከራሳቸው አልፈው ሀገርን እያሰቡ ያለሙት ሰብል ለመሰብሰብ መድረሱንም ገልጸዋል።
ሰብሉን ለመሰብሰብ ልማዳዊ በኾነው የሰው ኃይል ብቻ የማይቻል ስለመኾኑ አርሶ አደሩ አንስተዋል። ዘመናዊ የሰብል መሰብሰቢያ ማሽን ተጠቃሚ የመኾን ፍላጎት አለኝ ነው ያሉት። መንግሥት እና ባለሃብቶች በኮምባይነር አቅርቦት በኩል እገዛ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡
አርሶ አደሩ ከጤፍ በተጨማሪ ማሾ እና የምግብ ገብስ መዝራታቸውን እና ለመሰብሰብ መድረሱንም ነግረውናል፡፡
በሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አበበ ጌታቸው በዞኑ 490 ሺህ ሔክታር መሬት በሰብል መሸፈኑን ተናግረዋል። የደረሱ ሰብሎች ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ፣ በተባይ እና መሰል ችግሮች እንዳይበላሹ ለመሰብሰብ ጥረት እየተደረገ ስለመኾኑም ገልጸዋል።
አቶ አበበ በዞኑ 50 በመቶ የሚኾነውን የጤፍ ማሳ የመሰብሰቢያ ጊዜው ደርሷል ብለዋል። በወቅቱ ለመሰብሰብ ጥረት እየተደረገ እንደኾነም አስረድተዋል፡፡ ማሾ እና የምግብ ገብስም የመሰብሰብ ሥራ መጀመሩንም ነግረውናል፡፡
እስካሁንም በ35 ሺህ ሄክታር ማሳ ላይ ያረፈ አጠቃላይ ሰብል ተሰብስቧል። 8ሺህ 450 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሰብልን የመውቃት ሥራም ስለመከናወኑም ገልጸዋል።
አቶ አበበ በዞኑ 23 ወረዳዎች የደረሰውን ሰብል በሰው ጉልበት ብቻ መሰብሰብ እንደማይቻል ተናግረዋል። ኮምባይነር እና መሰል የግብርና መሣሪያዎችን ከአጎራባች ወረዳዎች ለመጠቀም ከአጎራባች ወረዳዎች እየተዋዋሱ ለመጠቀም ጥረት እየተደረገ እንደኾነም ገልጸዋል፡፡
የሰብል መሰብሰቢያ መሣሪያዎች ያሏቸው ወረዳዎች ፈጥነው መሰብሰብ ላይ እንደሚገኙ አቶ አበበ ጠቁመዋል። በመቀጠልም ማሽኑን ወደ ቀሪዎቹ አጎራባች ወረዳዎች ፈጥኖ በማስገባትም የሀገር ሃብት የኾኑ ሰብሎችን ሳይበላሹ ለመሰብሰብ ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ምርት እንዳይባክን እና ለሀገር እንዲተርፍ ለማድረግ የእያንዳንዱ አርሶ አደር ጥረት ወሳኝ መኾኑን አቶ አበበ ገልጸዋል። አሁን የደረሱትን ሰብሎች ጨምሮ ወደፊት የሚደርሱትንም በሚገባ ለመሰብሰብ የአየር ትንበያ መረጃዎችን እየተቀበሉ ጥረት ማድረግ እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡
እንደ ዞን የአየር ትንበያ መረጃዎችን እያዩ ምርት የመሰብሰብ ሥራ እያከናወኑ ስለመኾኑም አቶ አበበ አብራርተዋል።
ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!