“ፓን አፍሪካኒዝምን ቀድማ ያቀነቀነች ሀገር ልጆች ኾነን እርስ በእርስ መጋጨት ለታሪካችን አይመጥንም” ወጣቶች

35

ደሴ: ጥቅምት 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል ችግሮች ከተነሱ ሰነባብተዋል። በክልሉ የተፈጠረው ችግር መደበኛ እንቅስቃሴ እንዳይኖር ከመገደብ ጀምሮ ሌሎች ጫናዎችን አሳድሯል።

በክልሉ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ደግሞ የሁሉንም ድርሻ እንደሚጠይቅ ሲገለጽ ቆይቷል። ሁሉም በሚችለውና ልክ የመፍትሔ እጁን ቢዘረጋ የክልሉ ችግር ይፈታል፤ ጥያቄዎችም ይመለሳሉ ይላሉ።

በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉ ወጣቶችም የክልሉን ችግር ለመፍታት ውስጣዊ አንድነትን ማጠንከር፣ ለጋራ ችግሮች የጋራ አረዳድ እና የጋራ መፍትሔ መፈለግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ከድር አሊ ክልሉን ካጋጠመው ወቅታዊ ችግር ለማውጣት ብዙ ማሰብና ማንሰላሰል ይጠይቃል ብሏል። ጥያቄዎች የሚቀርቡበት አግባብ ሕጋዊ ሥርዓት መያዝ አለባቸው፤ ጥያቄ የሚቀበለውም አካልም በሥርዓት እና በሕግ አግባብ መቀበል አለበት ይላል። ሁለቱ ካልተጣጣሙ አላስፈላጊ ችግር ይፈጠራል ነው ያለው።

የሚቀርቡ ጥያቄዎች በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜያት የሚመለሱ ሊኾኑ እንደሚችሉም ተናግሯል። የረጅሙን በአጭር ጊዜ ካልተመለሰ ማለት እና በአጭር ጊዜ የሚመለሰውንም ለረጅም ጊዜ ማዘግየት አግባብ አይደለም ብሏል።

ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ማሰብ፣ ማንሰላሰል እና መወያየት ግድ እንደሚልም አንስቷል። ጥያቄ ተቀባዩ አካልም ጥያቄዎችን ቸላ ማለት እንደማይገባው እና ለጥያቄዎች ትኩረት መስጠት እንደሚገባው ተናግሯል።

በስክነት በመወያየት ችግሮችን መፍታት ካልተቻለ መጠፋፋቱ እንደሚቀጥልም ገልጿል። የሰከነ ውይይት በየደረጃው መካሄድ ይገባዋልም ብሏል። የክልሉ ጉዳይ ያገባኛል ለሚል ሁሉ የውይይት እድል መስጠት እንደሚገባም ተናግሯል።

ሚዛናዊ አካሄድ ችግሮችን በደንብ ለመረዳትና ለመፍታት ያስችላልም ብሏል። የሕዝብ ጥያቄዎች መደበቅና ማድበስበስ አይገባም ብሏል። ፖለቲከኞች ለችግሮች መፍቻ የሚኾኑ የተጠኑ ሃሳቦችን ይዘው መቅረብ እንደሚገባቸውም አመላክቷል።

ሀገር ከገባችበት ችግር በዘላቂነት ለማውጣት የችግሮችን ምንጭ እና መፍትሔዎችን የሚያመላክት ጥናት መሥራት እንደሚገባም አንስቷል።

ከችግር በዘላቂነት ለመውጣት ወደ ችግር ያስገባንን ጉዳይ መተው ይገባናልም ብሏል። ወደ ችግር ያስገቡንን ሳንተው ከችግሮች መውጣት አይቻልም ነው ያለው።

ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና አንድነት ከታሰበ ከብሔር አደረጃጀት የወጣ ሥርዓትን መተግበር ይገባል ብሏል። ፓን አፍሪካኒዝምን ያቀነቀነች ሀገር ልጆች ኾነን በብሔር መጋጨት ለታሪክ እንደማይመጥንም አመላክቷል።

ሌላኛው ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረገው ስንታየሁ ሸዋ ችግሮች እንዲፈቱ የአማራ ክልል ፖለቲካ ወጣቶችን ታሳቢ ያደረገ መኾን እንደሚገባውም ገልጿል። የአማራ ሕዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በአግባቡ ለማስመለስ በስክነት መመልከት ይገባል ነው ያለው።

በክልሉ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የክልሉ መንግሥት የሕዝቡ ጥያቄዎች ምላሽ በምን ደረጃ ላይ መኾናቸውን በየጊዜ ግልጽ ማድረግ ይገባል ነው ያለው።

የብዙኀን መገናኛ ድርጅቶችም የሕዝብን ጥያቄ በማንሳት መፍትሔ አመላካች ሥራዎችን መሥራት ይገባቸዋልም ብሏል። ሚዲያዎች ምክንያታዊ ወጣቶችን ለመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸውም ተናግሯል።

የሲቪክ ማኅበራትም ማኅበረሰብን ማንቃት፣ ማብቃት እና መገንባት አለባቸው ነው ያለው። በትብብር መሥራት ከተቻለ ሀገርን መገንባት እንደሚቻልም ገልጿል።

ችግሮችን ለመፍታት የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ከጠብ አጫሪና ተንኳሽ ንግግሮች መቆጠብ መቻል አለባቸውም ብሏል። ለትውልድ ግንባታ አስተዋጽኦ ያለው እና ምክንያታዊ የኾነ ወጣት እንዲፈጠር የሚያስችሉ ገንቢ ንግግሮችን ማድረግ ይገባቸዋል ነው ያለው።

ስሜታዊነት የተቀላቀለበትን የጥላቻ ንግግር ማስቆም ይገባልም ብሏል። ወጣቶችም በዘመናቸው አስደናቂ ታሪክ ለመፃፍ ፈተናዎችን በመጋፈጥና ሃሳቦችን በማመንጨት መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም ገልጿል። በሀገር ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ማሳደግም አለባቸው።

ኢትዮጵያን የሚመጥን ወጣት ለማፍራት ሰላማዊ ትግል እንደሚያስፈልግም አመላክቷል። ታላቋን ኢትዮጵያን ለመገንባት እስክብሪቶ እና ወረቀት ከመልካም ሃሳብ ጋር በቂዎች መኾናቸውንም ተናግሯል።

ወጣት ሰይድ ሙሐመድ ደግሞ በአማራ ክልል ያለውን ውስብስብ ችግር ለመፍታት ሰክነት እና እርጋታ እንደሚያስፈልግ ነው የተናገረው። ጥያቄዎች በአግባቡ እስኪፈቱ ድረስ ትዕግሥት ያስፈልጋልም ብሏል። ጥያቄዎችን ቆም ብሎ በማሰብና በማንሰላሰል ለመፍታት መሥራት እንደሚገባም አመላክቷል።

በክልሉ ያለውን ችግር በጋራ መፍታት ይገባልም ብሏል። አላስፈላጊ አካሄዶች ከችግሮች እንደማያወጡም ጠቁሟል።

በአግባቡ ያልተጠኑ እና ስልታዊ ያልኾኑ ጥያቄዎችን የማስመለሻ መንገዶች ለሌሎች አካላት መጠቀሚያ በማድረግ ችግሮች እንዳይፈቱ ያደርጋልም ብሏል። ጥያቄዎችን ለማስመለስ ትዕግሥት እና ጽናት እንደሚያስፈልግም አንስቷል።

ወጣቶች አቅማቸውን በበጎ ከተጠቀሙበት ሀገር ማልማት ይችላሉ፤ በመጥፎ ከተጠቀሙበት ደግሞ ብዙ ነገር ያበላሻሉ ነው ያለው። ወጣቶች ትዕግሥተኛ ሲኾኑ መንግሥት ደግሞ የወጣቶችን ትዕግሥት በመረዳት ለጥያቄዎች ተገቢ፣ ፈጣን እና ዘላቂ ምላሽ መሥጠት ይገበዋል ብሏል።

ራስን በራስ ማውደም አላስፈላጊ መኾኑንም ገልጿል። ሌሎች ክልሎች ሰላምና ልማት ላይ ናቸው ያለው ሰይድ ክልሉን የሰላም እጦት እና የኑሮ ውድነት እየፈተነው ነው ብሏል።

ሀገር ሰላም እንድትኾን ከግጭት መውጣት ይገባል ነው ያለው። ከእኔነት ስሜት ይልቅ እኛነት መንፈስን በማስረፅ ሀገርን በጋራ መገንባት አስፈላጊው ጉዳይ መኾኑንም ተናግሯል። እንወያይ፣ እንነጋገር፣ እንደማመጥ እንዲሁም በአንድነት እንሥራ ያን ጊዜ ችግሮቻችን ይፈታሉ ብሏል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሦስተኛ ዙር ጨዋታ ዛሬ ምሽት ባየር ሙኒክ ከጋላታሳራይ ዛሬ ማታ ይገናኛሉ።
Next articleየደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ ለመሰብሰብ ኮምባይነር እንደሚያስፈልጋቸው የሰሜን ሸዋ ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡