በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሦስተኛ ዙር ጨዋታ ዛሬ ምሽት ባየር ሙኒክ ከጋላታሳራይ ዛሬ ማታ ይገናኛሉ።

33

ባሕር ዳር: ጥቅምት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በምድብ አንድ የተደለደሉት ባየር ሙኒክ ከጋላታሳራይ እንዲሁም ማንቸስተር ዩናይትድ ከኮፕንሀገን ዛሬ ምሽት 1:45 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ፡፡

በተለይ የጀርመኑ ባየር ሙኒክ ከቱርኩ ጋላታሳራይ 52 ሺህ 600 ተመልካቾችን በሚይዘው በቱርኩ ራምስ ፓርክ ስታዲየም ይጫወታሉ፡፡

ዴይሊ ሜይል በድረ ገጹ እንዳስነበበው ባየር ሙኒክ በጀርመን ቡንደስ ሊጋ 11 ጨዋታዎችን ያሸነፈ ጠንካራ ቡድን ነው፡፡

ከተከላካይ እስከ አጥቂው መስመር ተጫዋቾቹ ተናበው የሚጫወቱ በመኾናቸው ማራኪ ጨዋታ ያሳያሉ ተብለው ይጠበቃሉ ብሏል፡፡

100 የሚኾኑ የሁለቱ ክለቦች ደጋፊ ያልኾኑ ቀንደኛ የእግር ኳስ ተመልካች ከሰጡት ድምጽ ውስጥ ባየር ሙኒክ አሸናፊ ይኾናል ያሉት 60ዎቹ መኾናቸውን ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡

በአንጻሩ ድምጽ ከሰጡት መካከል 40 በመቶ ያህሉ ጋላታሳራይ አሸናፊ ይኾናል ማለታቸውን ዴይሊ ሜይል ጠቁሟል።

የባየር ሙኒክ አሠልጣኝ ቶማስ ቱቸል ጋላታሳራይን አቅልለው እንደማይመለከቱት ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡

በሻምፒዮንስ ሊጉ ከኮፐንሃገን ጋር 2 አቻ ተለያይቶ፣ ማንቸስተር ዩናይትድን በኦልድ ትራፎርድ 3 ለ 2 መርታቱ የክለቡን ጥንካሬ ያሳያልና ብለዋል፡፡

የጋላታሳራዩ አሠልጣኝ ኦካን ቡሩ “ባየር ሙኒክ በጠንካራ፣ ንቁ እና ፈጣን ተጫዋቾች የተዋቀረ ክለብ በመኾኑ በተለየ ትኩረት ሳንፈራ ለማሸነፍ እንጫወታለን ብለዋል፡፡

ምድቡን ባየር ሙኒክ በስድስት ነጥብ ይመራዋል፤ ጋላታሳራይ በአራት ነጥብ ሁለተኛ ነው፤ ኮፕንሀገን በአንድ ነጥብ ሦስተኛ ሲኾን ማንቸስተር ዩናይትድ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን ደረጃ ይዟል፡፡

ዘጋቢ:- ሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለ7 የዩኒቨርሲቲው ምሁራን የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጠ።
Next article“ፓን አፍሪካኒዝምን ቀድማ ያቀነቀነች ሀገር ልጆች ኾነን እርስ በእርስ መጋጨት ለታሪካችን አይመጥንም” ወጣቶች