“ሁልጊዜ የሌሎች ሃሳብ ተከታዮች ብቻ ከመኾን ሃሳብ አመንጪዎች መኾን አለብን” ወጣቶች

50

ደሴ: ጥቅምት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ወጣቶችን በትክክለኛ ዓላማ የተጠቀሙ ሀገራት አዳዲስ ለውጦችን አሳይተዋል። በአንፃሩ ወጣቶችን ለሀገር የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ያልተረዱና ወጣቶችን በምጣኔ ሃብት፣ በማኅበራዊ እና በፖለቲካዊ አውዶች ታሳቢ ያላደረጉ ሀገራ ችግር ገጥሟቸዋል።

ኢትዮጵያ ወጣቶች የሚበዙባት ሀገር እንደኾነች ይነገራል። ወጣቶችን በተገቢው መልኩ ከተጠቀመች አንድነቷ የተጠበቀና የፀናች ሀገር ለመገንባት እንደሚያስችላት ይታመናል።

በአንፃሩ ወጣቶችን ለሀገራቸው የሚያበረከቱትን አስተዋጽኦ የዘነጋ አካሄድ ካለ፣ ወጣቶችም ለሀገራቸው የሚኖራቸውን አስተዋጽኦ አለመረዳትና ለሀገራቸው አስበው አለመሥራት ከተፈጠረ የኢትዮጵያ ችግሮች ውስብስብ ይኾናሉ የሚሉት በርካቶች ናቸው።

ምክንያታዊ እና ለምን የሚሉ ወጣቶች በተፈጠሩ ጊዜ የሀገር ችግሮቿ እያነሱ ተስፋዎቿ እየገዘፉ ይሄዳሉ። ለምን የሚሉ ጠያቂ፣ በምክንያት የሚያምኑ እና በምክንያት የሚያሳምኑ ወጣቶች ገንቢ የኾኑ ሀሳቦችን በማመንጨት ሀገርን ይጠቅማሉ።
አሚኮ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከወጣቶች ጋር ቆይታ አድርጓል።

የደሴ ከተማ ነዋሪው ከድር አሊ ምክንያታዊ የኾኑ ወጣቶች ከጥሩ ቤተሰብ፣ ከጥሩ ጎረቤትና ከጥሩ ማኅበረሰብ ይቀዳሉ ይላል። ምክንያታዊ ወጣቶችን የሚፈጥሩ ማኅበራዊ ስሪቶች በተናጉ ጊዜ ደግሞ ምክንያታዊ ሳይኾን ምናባዊ ወጣቶች ይፈጠራሉ።

ምክንያታዊ ወጣቶችን ለመፍጠር የቆዩ መልካም ማኅበራዊ ስሪቶች ትልቅ ድርሿ እንዳላቸው ተናግሯል። ሰው የሰውነት መለኪያዎች አሉት የሚለው ከድር ሰውነትን መሠረት ያደረገ ሰው የቤተሰብ፣ የማኅበረሰብ እና የሀገርን ኀላፊነት የሚረዳና ኀላፊነቱንም የሚወጣ ነው ይላል።

ለምን ብሎ የሚጠይቅ፣ በምክንያት የሚያምን ልጅ እንዲኖር ወላጅ ታላቅ ኀላፊነት አለበት። ወላጆች፣ ማኅበረሰብ እና መንግሥት ምክንያታዊ ወጣቶችን የመቅረጽ ትልቅ ኀላፊነት እንዳለባቸውም ተናግሯል። እኔ ምን አገባኝ የሚል አካል ካለ ትውልዱም ምክንያታዊ አይኾንም። ቆይቶ በሀገር ላይ ለሚፈጠረው ችግርም ተጠያቂ ነው ብሏል።

የትውልድ ግንባታ ከታች ወደላይ በሽግግር መኾን እንደሚገባውም ተናግሯል። ደክሞ ማግኘት ሳይኾን ሳይደክሙ መቀበል የለመደ ትውልድ መፍጠር ለሀገር ግንባታ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለውም ገልጿል። ራሱን የቻለ፣ የሚጠይቅ እና የተስተካከለ አካሄድ ያለው ትውልድ መፍጠር ይገባልም ብሏል።

ከመገዳደል፣ ከመጠላለፍ እና አንደኛው በአንደኛው ላይ ከመነሳት አስተሳሰብ መውጣት እንደሚገባም ተናግሯል። ዘመኑ እና ማኅበረሰቡ የሚፈልገውን ሃሳብ ማምጣት ከዚህ ዘመን ትውልድ እንደሚጠበቅም አመላክቷል።

ማኅበረሰቡ ከባሕል፣ ከታሪክ፣ ከሃይማኖት እና ከእሴት የወጣ ትውልድ እንዳይኖር መግራት ይገባዋልም ብሏል። ማኅበረሰቡ ከመሠረቱ ጀምሮ ትውልድን መቅረጽ ካልቻለ ትውልዱን የባከነ ነው ብሎ መውቀስ እንደማይችልም አመላክቷል።

የአንድን ዘመን ትውልድ የተሻለ ለማድረግ ሁሉም ኀላፊነት እንዳለበት ገልጿል። በእያንዳንዱ የማኅበረሰብ ክፍል ጥያቄና ፍላጎት አለ የሚለው ከድር ጥያቄዎችን ለማስመለስ በትክክለኛው መንገድ መታገል ይገባዋል ብሏል።

ማኅበራዊ ሚዲያ ሊያፈርሳቸው የሚታትረውን ድንቅ የማኅበረሰብ እሴት መጠበቅ ይገባል ነው ያለው። የማኅበረሰብ እሴት ሲፈርስ ደግሞ የከፋ ችግር በሀገር ላይ ይመጣል።

ሌላኛው የደሴ ከተማ ወጣት ስንታየሁ ሸዋ ጥብቅ ማኅበራዊ እሴቶች ምክንያታዊ ወጣቶችን ይፈጥራሉ ነው ያለው። ምክንያታዊ የኾኑ ወጣቶችን ለመፍጠር በሀገር የሚተገበረው ሥርዓትም ድርሻ እንዳለው ተናግሯል።

ወጣቶችን ታሳቢ ያላደረገ ሥርዓት ካለ ተዘነጋሁ የሚል ስሜት እንዲኖራቸው ያደርጋልም ብሏል። ምክንያታዊ ወጣቶችን ለመፍጠር የሀገርን ባሕል፣ እሴትና ታሪክ የተመረኮዘ ፖለቲካዊ ሥርዓትን ማስፋት ይገባል።
የሌሎች ሀገራትን ፖለቲካዊ ሥርዓት እንዳለ መጫን ምክንያታዊ ያልኾኑ ወጣቶች እንዲፈጠሩ በር እንደሚከፍትም አንስቷዋል።

መንግሥት ሀገር ወዳድ ወጣት ትወልድ መፍጠር ግድ እንደሚለውም ተናግሯል። በኢትዮጵያ ታሪክ መንግሥታት ሀገርና ሠንደቁን እንዲያከብር፣ ታማኝ፣ በአንድነት የሚያምን፣ ጽኑ፣ ቅን፣ ሀገርን የሚያስቀድም ትውልድ እንዲፈጠር ይሠሩ እንደነበር ያስታወሰው ስንታየሁ የቀደመው መልካም አካሄድ ቀርቶ ለቁስ የሚገዛ ትውልድ እንዲፈጠር ኾኗል ብሏል።

መልካም እና ዘመናትን የተሻገሩ እሴቶች ላይ ትኩረት አድርጎ አለመሥራት ምክንያታዊ ያልኾነ ትውልድ እንዲፈጠር እንደሚያደርግም ተናግሯል። በሥነ ምግባር እና ግብረ ገብነት ተኮትኩተው ያደጉ ወጣቶች ታላላቅ ደረጃዎች ላይ ሲደርሱ መኖራቸው እና ሀገር ያስጠሩትም በዛ መንገድ የመጡ ናቸው ብሏል።

የተዛባ ትርክት መኖር እና ያልተገባ አስተምህሮ ለትውልዱ ማስተማር ትውልዱን በእጅጉ እየጉዳው መኾኑንም ገልጿል። ሀገር ወዳድነትን፣ አንድነትን እና ለሀገር ሟችነትን በልኩ ማስተማር እንደሚገባም ተናግሯል።

የጥላቻና የቂም በቀል ፖለቲካ ከምክንያት ይልቅ ስሜት የሚነዳው ትውልድ እንዲፈጠር አድርጓል። የመገዳደል እና የፉከራ ፖለቲካ ወጣቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯልም ብሏል። መልካም ነገሮችን ማስፋት የተሻለ ትውልድ እንዲፈጠር ያደርጋል ነው ያለው። ዜጎቿን በሚገባ የምትጠቀም ሀገር ታድጋለች።

ለሀገር የሚጠቅም፣ አንድነትን የሚያመጣ ፖለቲካ እና ፖለቲከኛ እንደሚያስፈልግም ገልጿል። ለወጣቶች የሥራ እድል አለመፍጠር እና ወጣቶችን በአግባቡ አለመጠቀም ለግጭት መነሻ እንደኾነም አንስቷል። የሥራ እድል የተፈጠረለት ወጣት ለጥልና ለጥላቻ ጊዜ እንደሌለውም ተናግሯል። የኑሮ ውድነት እያሳደረው ያለው ጫና ሌላኛው የግጭት መንስኤ ሊኾን እንደሚችልም አመላክቷል።

የቀደሙ እሴቶች ትወልድን ለማስተካከል፣ ሥርዓት አክባሪ እንዲኾን ለማድረግ ትልቅ ድርሻ አላቸው የሚለው ስንታየሁ አሁን አሁን እሴቶችን የመተግበር እና የማስተግበር ችግር አለ ብሏል። የሃይማኖት ተቋማትም ማስተማር የሚገባቸውን ጉዳይ እያስተማሩ አይደለም ነው ያለው።

ሀገርን ለማሳደግ የሚጥር፣ ለነገ የሚያስብ ወጣትን ለመፍጠር ሁሉም በትኩረት መሥራት ይገባዋልም ብሏል። አሁን ላይ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ሰብዓዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች አሉብን የሚለው ስንታየሁ ችግሮችን ለመሻገር በትኩረት መሥራት እና መወያየት እንደሚገባም አመላክቷል።

ሀገርን በአንድነት እና በእኩልነት ከፍ ለማድረግ ውይይት ወሳኙ ጉዳይ መኾኑንም አንስቷል። የእርስ በእርስ ግጭቱ የትም እንደማያደርስም ተናግሯል። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ማንነት አለው፣ በማንነቱ መኖር ይችላል፣ የብሔርተኝነት አስተሳሰብ ለትውልዱ ፈተና ኾኖበታልም ብሏል።

እንደ ስንታየሁ ገለፃ ኢትዮጵያ የሁሉንም ብሔር የምትወክል ሁሉንም አንድ የምታደርግ ናት፣ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት በአንድነት ኖረዋል፣ አሁን ፈተና የኾነው የተወሰኑ ፖለቲከኞች እና ጥቅም ፈላጊዎች አካሄድ ነው።

የኢትዮጵያን ፖለቲካ ከኢትዮጵያ ባሕል፣ ታሪክ እና እሴት ጋር የተዛመደ ማድረግ ችግሮችን ለመፍታት ቁልፍ እንደሚኾንም ገልጿል።

ሰይድ ሙሐመድ ደግሞ ምክንያታዊ ሰው ለሚያነሳቸውና ለሚነሱበት ነገሮች እንዴ እና ለምን ብሎ ይጠይቃል ነው ያለው። አንድ ሰው ለሚያነሳቸው ጉዳዮችና ለጉዳዮቹ መልስ ለማግኘት በተለያየ መንገድ ማየት እንደሚገባውም አንስቷል። አንድን ጉዳይ ከማድረግ አስቀድሞ ሊኖረው የሚችለውን ጥቅምና ጉዳት መመዘን ይገባል።

ምክንያታዊ ሰው እምነቱንና ማንነቱን የሚያከብር እና የሌሎችን ማንነት ጠንቅቆ የሚያውቅ ነውም ብሏል። ምክንያታዊ ሰው የሚኖርበትን ማኅበረሰብ እና የተነሳባትን ዓላማ ጠንቅቆ እንደሚያውቅም አንስቷል።

በኢትዮጵያ ምክንያታዊ የኾኑ እና ምክንያታዊ ያልኾኑ ወጣቶች መኖራቸውንም ገልጿል። ነገር ግን ይላል ሰይድ ምክንያታዊ የኾኑ ሰዎች ምክንያታዊ ባልኾኑት ተውጠው ሃሳባቸው እንዳይጎላ እየተደረጉ ነው።

ወጣቶችን ምክንያታዊ እንዳይኾኑ እያደረጋቸው ያለው ጉዳይ ሁልጊዜ የሌሎች ሰዎች ተከታይ የመኾን ጉዳይ መኾኑንም አመላክቷል። ያለፈን ነገር ከመውቀስ እና ዛሬን በትናንት ምክንያት ከማበላሸት ይልቅ በራስ አቅም ዛሬን ማሳመር ይገባል ብሏል።

ሁልጊዜ የሌሎች ሰዎች ሃሳብ ተሸካሚዎች ኾኖ መኖር እንደማይገባም ገልጿል። ፈጣሪ የማገናዘቢያ አዕምሮ ሰጥቶናል የሚለው ሰይድ የራስን አዕምሮ በመጠቀም ሁልጊዜ ከሌሎች ተከታይነት መላቀቅ ይገባል ነው ያለው።

የዚህ ዘመን ትውልድ በብዛት ያለፉትን በመውቀስ የተጠመደ መኾኑንም ገልጿል። ካለፈው አለመማር ምክንያታዊነት እንዳይኖር እያደረገ መኾኑን እና ሀገርም በችግር ውስጥ እንድትቀጥል ማድረጉን ነው የተናገረው። ካለፉት ጊዜያት መማር ካልቻልን ችግሮቻችን እየባሱ፣ ፈተናዎቻችን እየበረከቱ ይቀጥላሉ ብሏል።

በኢትዮጵያ ሁለት መሠረታዊ ችግሮች አሉ የሚለው ሰይድ አንደኛው ፍፁም መጥላት እና ሁለተኛው ደግሞ ፍፁም አድርጎ መውደድ ናቸው። እንደ ሰይድ ገለፃ አንድ የምንወደው ፖለቲከኛ ከተናገረ ፍፁም ትክክል፣ ተሳስቶ እንደማያውቅ፣ ሁልጊዜ እርሱ ብቻ ነው ለሀገርና ለሕዝብ የሚያስብ በሚል ገደል ቢገባም ተከትለነው እንገባለን፣ ይህ አካሄድ ምክንያታዊ እንዳንኾን አድርጎናልም ነው ያሉት።

የፖለቲካው ሥርዓት ብልሹነት እና ገሚሱን አንጋሽ፤ ገሚሱን ወቃሽ ማድረግ ሀገሪቱን ፈተና ውስጥ እንደከተታትም ገልጿል። በእስልምና አስተምህሮ ብሔርተኝነት ጥንብ ናት ተዋት ትባላለች የሚለው ሰይድ ብሔርተኝነትን በመተው ሰውነትን ማስቀደምና እኩልነትን ማንገስ ይገባል ነው ያለው።

በተለይም በዚህ ዘመን በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሠራጩ መረጃዎችን አሜን ብሎ መቀበል ምክንያታዊ ያልኾነ ወጣት እንዲፈጠር አድርጓታልም ብሏል። ወጣቶች ለሚነሱላቸው ጥያቄዎችም ኾነ ለሚመጡባቸው ችግሮች ምክንያታዊ ኾነው መቆም ይገባቸዋል ነው ያለው።

በታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጥንታዊዉን የጋፋት ኢንዱስትሪ መንደር በማልማት የቱሪዝም ኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማጎልበት ሁሉም ሊረባረብ ይገባል” የደቡብ ጎንደር ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ።
Next articleአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለ7 የዩኒቨርሲቲው ምሁራን የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጠ።