“ጥንታዊዉን የጋፋት ኢንዱስትሪ መንደር በማልማት የቱሪዝም ኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማጎልበት ሁሉም ሊረባረብ ይገባል” የደቡብ ጎንደር ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ።

48

ባሕር ዳር: ጥቅምት 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር ዞን ደብረታቦር ከተማ አቅራቢያ የሚገኘውን ጥንታዊውን የጋፋት ኢንዱስትሪ መንደር በማልማት የቱሪዝም ኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማጎልበት እንደሚገባ ተገልጿል።

አጼ ቴዎድሮስ ከሚታወሱባቸው ታሪካቸው ውስጥ አንዱ ሴባስቶፖል መድፍና የኢንዱስትሪ መንደራቸው ጋፋት ነው። ንጉሡ ኢትዮጵያን ከዘመነ መሣፍንት ክፍፍል አላቅቀው አንድነቷን ለማጠንከር አስበው ተግብረውታልም። ሀገራቸውን ለማሠልጠን ቀን ከሌት ያልሙ ነበር። የወቅቱ የኢትዮጵያ ዳርቻ የነበሩትን ምጽዋና ዘይላን ከቱርኮች ለማስለቀቅ እና ወደ ኢየሩሳሌም ለመዝመትም ይመኙ ነበር። እናም የጦር መሣሪያ ለማምረት እንግሊዞችን ጠየቁ።

ለጠየቁት ሕዝቤን አሠልጥኑልኝ ጥያቄ እና የመሣሪያ ፍላጎት ተግባራዊ ምላሽ ሲያጡ ቆንስላዎችንና ሚሲዮኖችን በማሰር እርምጃ ወሰዱ።

በእስር የያዟቸውን የእንግሊዝ ፣ የጀርመንና ሌሎችም ዜጎች በጋፋት መድፍ እንዲሠሩላቸው አዘዙ። ነገደ ጋፋት የሚባሉ የእጅ ጥበብ ሙያተኞች ደግሞ ከመናገሻቸው ደብረታቦር ከተማ በስተሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ 6 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ኅሩይ አባ አረጋዊ በሚባል ቀበሌ ውስጥ ይገኛሉ። ለመድፍ መሥሪያ የሚኾን የብረት አፈርም አካባቢው የታደለ ነው።

ለመጀመሪያ ጊዜ የተሠራውን መድፍ ሴባስቶፖል ብለው ሰየሙት። መድፉን እያስጎተቱ በጥቅምት 1860 ዓ.ም ጉዞ ተጀምሮ በመጋቢት መቅደላ አፋፍ መድረሳቸውን ተክለጻድቅ መኩሪያ በ1981 ዓ.ም ባሳተሙት ”ዐጼ ቴዎድሮስ እና የኢትዮጵያ አንድነት” መጽሐፋቸው ተንትነዋል።

ጋፋት የኢንዱስትሪ መንደር የኢትዮጵያ ቀደምት ሥልጣኔ እና የመሪዎቿን ሀገርን የማዘመን ታላላቅ ህልሞች አንዱ መገለጫ የኾነው የሴባስቶፖል መድፍ መፈብረኪያ ቦታ ነው።

በጋፋት የኢንዱሥትሪ መንደር ለመድፍ መሥሪያ ያገለገሉ ቁርጥራጭ ብረቶች ዘመን ቢፈራረቅባቸውም ከአፈር ጋር ተደባልቀው ዛሬም ድረስ ይታያሉ። በዚያን ዘመን አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ ቤቶች ፍርስራሻቸው ጨርሶ አልጠፉም።

ይህ የኢትዮጵያ የሥልጣኔ አሻራ ዛሬ ላይ በ1 ነጥብ 8 ሄክታር መሬት ተከልሏል። ነገር ግን ከመታጠር ባለፈ ትውልድ በልኩ እየዘከረው አይደለም። በቱሪስት መስህብነት ገቢ እያስገኘ አለመኾኑንም የደቡብ ጎንደር ዞን ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ የቱሪስት መዳረሻ ልማት ባለሙያው ሲሳይ ገደፋው ያብራራሉ።

ትልቅ ታሪክ እና የሥልጣኔ ዱካ ያረፈበት ጋፋት የታሪኩን ግዝፈት ያክል እንዳልለማና የቱሪስት መዳረሻ እንዳልኾነ ነው አቶ ሲሳይ የተናገሩት።

እንደ አቶ ሲሳይ ማብራሪያ የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የዐጼ ቴዎድሮስን የዕውቀት ጥያቄ የመመለሥ ራዕይን ሰንቆ እየሠራ ነው። ጋፋት የኢንዱሥትሪ መንደርንም አልምቶ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እየሠራ ይገኛል ነው ያሉት።

ደብረታቦር ዩኒቨርስቲ፣ የደቡብ ጎንደር ዞን አሥተዳደርና የመከላከያ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን የካቲት 2013 ዓ.ም ታሪካዊውን የኢንዱስትሪ መንደሩርን መልሶ የማቋቋም ፕሮጀክት ስምምነት መፈራረማቸውም ይታወሳል። ባለፉት ዓመታት ያጋጠመው የሰላም ችግር ተቋማቱ ወደ ተግባራዊ ሥራ እንዳይገቡ ማደናቀፉም አቶ ሲሳይ ተናግረዋል። ሰላም እና መረጋጋት ሲፈጠር ቦታውን ማልማት እንደሚጀመርም ገልጸዋል።

ለአካባቢው ማኅበረሰብ በተለይ ለወጣቶችና ተማሪዎች ጋፋትን ለማስተዋወቅ እየሞከርን ነው ያሉት አቶ ሲሳይ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግም ሰፊ ሥራ እንደሚፈልግ ነው የገለጹት።

“ጥንታዊውን የጋፋት ኢንዱስትሪ መንደር በማልማት የቱሪዝም ኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማጎልበት ሁሉም ሊረባረብ ይገባል” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። ለታሪካዊው ኢንዱሥትሪ መንደር መሰረተ ልማት እንዲሟላለት ቢደረግ ተማሪዎችና ወጣቶች አካባቢያቸውንና ታሪካቸውን ለማወቅ ያስችላቸዋል፤ ገብኝዎችን መሳብና ማቆየት ይቻላል ነው ያሉት።

ቱሪዝም በባህሪው ሰላም ይፈልጋል ፤ ሰላም ካለ ጎብኚ ይኖራል፤ ጎብኚ ሲኖር ደግሞ የሥራ ዕድል ይፈጠራል ነው ያሉት አቶ ሲሳይ። ኅብረተሰቡም ከቱሪዝሙ ለመጠቀም ለሠላም መስፈን እና ለታሪካዊ ቅርስ መስህቦቹ መልማት ሊተባበር እንደሚገባ አሳስበዋል።

ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleስመ ገናናነቱን ያጣው አያክስ አሠልጣኙን አሰናበተ።
Next article“ሁልጊዜ የሌሎች ሃሳብ ተከታዮች ብቻ ከመኾን ሃሳብ አመንጪዎች መኾን አለብን” ወጣቶች