
ባሕር ዳር: ጥቅምት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአያክስ አምስተርዳም ክለብ ከውጤት ማሽቆልቆል ጋር በተያያዘ ከአሠልጣኝ ሞሪስ ስቴጅ ጋር የነበረውን ውል ማቋረጡን አስታውቋል።
በኔዘርላንድ ሊግ ኢሬዲቪዚ ታሪክ የአያክስ ክለብ ሰላሳ ስድስት ጊዜ በማሸነፍ ባለደማቅ ታሪክ ነው፡፡ አራት ጊዜ ደግሞ የአውሮፓ ክለቦች ባለድል መኾኑን ቢቢሲ አስታውሶ፤ ክለቡ ለበርካታ ዓመታት ገናናነቱን አስመስክሯልም ብሏል፡፡
ነገር ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አያክስ የሚታወቅበት ገናናነቱ ከድቶታል።
የአያክስ ክለብ አሥተዳዳሪዎች ለስካይ ስፖርት እንዳሉት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ክለቡ ውጤት እየራቀው እና እየደበዘዘ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የክለቡን አሠልጣኝ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ አልተወጡም በሚል ወቅሰዋል፡፡
ለአብነትም አያክስ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ከኤፍሲ ዩትሬክት ክለብ ጋር በነበረው ጨዋታ 4 ለ 3 ተሸንፏል። በውድድር ዓመቱ ሰባት ጨዋታዎችን አድርጎ በአምስት ነጥብ ከ18 ክለቦች በ17ኛ ደረጃ ላይም ተቀምጧል፡፡
በመጨረሻም የክለቡ ኃላፊዎች እና አሠልጣኙ ሞሪስ ስቴጅ ተወያይተው ተለያይተዋል። ሞሪስ ስቴጅም አያክስን ወደ ቀደመ ገናናነቱ ለመመለስ ሁሉንም ነገር ማድረጋቸውን አስታውሰው ፤ ውጤታማ ባለመኾናቸው ማዘናቸውን እና ሥራቸውን መልቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡
ክለቡም ከአሠልጣኙ ጋር በስምምነት መለያየቱን ይፋ አድርጓል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!