”በ2016 በጀት የክልሉን ሕዝብ ሙሉ በሙሉ የጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲኾን እየተሠራ ነው” የአማራ ክልል ጤና ቢሮ

47

ባሕር ዳር: ጥቅምት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎት ዜጎች በዓመት አንድ ጊዜ ከፍለው ዓመቱን በሙሉ የጤና አገልግሎት የሚያገኙበት የጤና ሥርዓት ነው።

አቶ እዉነቱ ተረፈ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ባሶሊበን ወረዳ የጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚ የኾኑ አርሶ አደር ናቸው። አገልግሎቱ ከፍተኛ የጤና ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል። በዝቅተኛ ወጭ የእርሳቸውን እና የቤተሰቦቻቸውን የጤና ኹኔታ ያሻሻለ አሠራር ስለመኾኑም ተናግረዋል።

አርሶ አደሮች አገልግሎቱ ጠቃሚ ቢኾንም ውስንነቶች እንዳሉበትም ጠቅሰዋል።

👉 በሕክምና ጊዜ ለጤና መድኅን ተጠቃሚው ፈጣን አገልግሎት አለማግኘት፣

👉 መድኃኒት የሚገኘው አብዛኛውን ጊዜ ከግል ፋርማሲዎች መኾኑ እና
👉 ከግል መድኃኒት ቤት ሲገዙ ለከፈሉት ገንዘብ የሚመለስላቸው የወጪያቸውን ሲሦ ያክል ብቻ መኾኑን በውስንነት ጠቁመዋል።

”በቀበሌ ምክር ቤት ውይይታችን ጥያቄውን እናነሳለን፤ ግን ለሚመለከተው አካል የሚደርስልን አይመስለኝም” በማለት አርሶ አደሩ ተናግረዋል። የሚፈጠሩ የአሠራር ውስንነቶች ተቀርፈው ፈጣን የሕክምና አገልግሎት መሰጠት ከተቻለ ጤና መድኅን ሁነኛ የአርሶ አደሮች የሕክምና አማራጭ መኾኑንም ገልጸዋል።

በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የሃብት አሰባሰብ፣ አሥተዳደርና አጋርነት ዳይሬክተር አዲሱ አበባው አገልግሎቱ በተጠቃሚ ሽፋንም ኾነ በአተገባበሩ እያደገ መኾኑን ተናግረዋል።

በዓለም ጤና ድርጅት መስፈርት አንድ ሰው በዓመት ከሁለት እስከ ሦስት ጊዜ ያለበትን የጤና ደረጃ ለማወቅ የጤና ተቋምን መጎብኘት እንዳለበት ይመከራል። በአማራ ክልል የጤና መድኅን አገልግሎት ከመጀመሩ በፊት 0 ነጥብ 2 የነበረው የመታከም ዕድል ከጤና መድኅን ትግበራ በኋላ ወደ 1 ነጥብ 8 ማደጉንም አቶ አዲሱ አመላክተዋል።

እስካሁን ድረስ 17 ነጥብ 8 ሚሊየን የሚኾነው የክልሉ ሕዝብ የጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚ መኾኑንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

አቶ አዲሱ ”የጤና መድኅን ታካሚ ስለሚበዛና ሰልፍ ስለሚኖር አገልግሎቱ ፍጥነት ላይኖረው ይችላል” ብለዋል። የግል መድኃኒት ቤቶች እና የጤና ተቋማት አገልግሎት እንዲያቀርቡ ውል ተይዞ የጤና መድኅን ሕክምና እየተሰጠ ስለመኾኑም አንስተዋል። በዚህ አሠራርም 120 ወረዳዎች ከግል የጤና ተቋማት ጋር ዉል ይዘው መሥራት መጀመራቸውን ገልጸዋል። በዚህም ብልሹ አሠራርን፣ የታካሚውን እንግልትና ወጪም ማስቀረት ተጀምሯል ብለዋል።

ዳይሬክተሩ “በ2016 በጀት ዓመት የአማራ ክልል ሕዝብ ሙሉ በሙሉ የጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲኾን እየተሠራ ነው” ብለዋል።

የጤና መድኅን አገልግሎቱን ውጤታማ በማድረግ የሕዝቡን ጤና ለመጠበቅ በአገልግሎቱ ተጠቃሚ መኾን የሚገባውን ሰው ብቻ ተጠቃሚ ማድረግ እና ጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጣቸውን በሕጉ መሠረት ብቻ መፈጸም እንደሚገባቸው አሳስበዋል። ይህ እንዲሳካ ደግሞ በክልሉ ሰላምን ማስፈን እና ከኅብረተሰቡ ጋር ውይይት ማድረግ አስፈላጊ ስለመኾኑ አቶ አዲሱ ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራና ኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተፈናቃዮችን መልሶ በማቋቋም ዙሪያ ምክክር አደረጉ።
Next articleስመ ገናናነቱን ያጣው አያክስ አሠልጣኙን አሰናበተ።