
ባሕር ዳር: ጥቅምት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ቡድን ባሕር ዳር በመገኘት ከአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ጋር ምክክር አድርገዋል።
ባለፉት ዓመታት ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎችና በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በቁርጠኝነት እየሠራ መኾኑን በምክክሩ ወቅት ተገልጿል።
በጥፋት ኀይሎች ጥቃት ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉና ሐብት ንብረታቸው የወደመባቸውን ወገኖችን በመለየት በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር አብረው ከኖሩት የኦሮሞ ሕዝብ ጋር አብሮነታቸውን ለማስቀጠል ቅንጅታዊ ጥረት እንደሚያስፈልግም ተወያይተዋል።
የሁለቱን ክልል ሕዝቦች አንድነትና አብሮነት የሚጻረሩ ኀይሎችን በመታገል የዜጎችን ደኅንነትና ሐብት ንብረት የማፍራት ነጻነትን ማረጋገጥ እንደሚገባም መግባባት ላይ ደርሰዋል።
ተፈናቃዮች እያሳለፉት ያለውን ችግር ያገናዘበ ፈጣን ስምሪት በመውሰድ ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እንዲመለሱ የማድረግ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዲደረግም አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!