
አዲስ አበባ: ጥቅምት 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎችን ለመደገፍ እና በቴክኖሎጂ የታገዘ ዓለም አቀፍ የገበያ ትስስር ለመፍጠር “ኔስት” የተባለ ብሔራዊ ኢኒሼቲቭ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በጋራ እያካሄደዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚንስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ.ር) በዓለማችን ላይ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች አዳዲስና ችግር ፈቺ የፈጠራ ሃሳቦችን በማመንጨት ግዙፍ ኢኮኖሚን እየገነቡ ነው ብለዋል። በሀገራችንም ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች በርካታ ሃሳቦችን ይዘው እየመጡ እንደኾነ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ የካፒታል እጥረት፣ የሚወጡ ፖሊሲዎች አለመተግበርና አሳሪ የሕግ ማዕቀፎች አለመሻሻል በዘርፉ ስር የሰደዱ ችግሮች መኾናቸውን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
እነዚህን ችግሮች ቀጣይነት ባለው መንገድ ለመፍታት እና ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ቴክኖሎጂን ተጠቅመው ምርቶቻቸውን ለዓለም ገበያ እንዲያቀርቡ ይሠራል ብለዋል።
ዛሬ የተጀመረው “ኔስት” የተባለ ብሔራዊ ኢኒሸቲቭም ሥራ ፈጣሪዎችን የሚያበረታታ እና የሀገርን ኢኮኖሚ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ወሳኝ መኾኑን ሚኒስትሩ አንስተዋል።
ዘጋቢ:- ቤተልሄም ሰለሞን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!