
ደብረ ብርሃን: ጥቅምት 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በከተማ አሥተዳደሩ በ2015 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል የሀገር አቀፍ ፈተናን ከወሰዱ 2 ሺህ 364 ተማሪዎች ውስጥ የማለፊያ ውጤት ያሥመዘገቡት 193 ተማሪዎች ብቻ ናቸው፡፡
ውጤቱ ከ2014 የተማሪዎች ውጤት ጋር ሲነጻጸር መቀነሱን የትምህርት መምሪያው የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ቡድን መሪ አሀዱ ቀፀላ ተናግረዋል፡፡
ቡድን መሪው ባለፋት ሁለት ዓመታት በ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ውጤት ላይ ያጋጠመውን የውጤት ማሽቆልቆል የሚቀለብሱ ሥራዎችን ለመሥራት ትምህርት መምሪያው አቅዶ ወደ ሥራ ገብቷል ብለዋል፡፡
“በትምህርት ጥራት ላይ እያጋጠሙ ያሉ ሥብራቶችን ለማከም ከቅድመ መደበኛ ትምህርት ጀምሮ በትኩረት መሠራት ይጠይቃል” ብለዋሎ አቶ አሀዱ ቀፀላ፡፡ ይኼንኑ ታላሚ ያደረጉ ሥራዎችን ለመሥራት መጀመሩንም አንስተዋል፡፡
በከተማ አሥተዳደሩ በሚገኙ 79 የመንግሥት እና የግል ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች 9 ሺህ 980 ሕጻናት ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ነው፡፡
ሕጻናቱን ከመሠረቱ ጀምሮ ለማብቃት በትኩረት እየተሠራ ነው ተብሏል። ቡድን መሪው በቅድመ መደበኛ ትምህርት ላይ በሙያው የሠለጠኑ መምህራን እጥረት፣ የመማሪያ ክፍል ውስንነቶች እና የግብአት ችግሮች አኹንም ለትምህርት ጥራቱ እንቅፋቶች መኾናቸውንም አንሥተዋል፡፡
ትምህርት መምሪያው የተለዩትን እጥረቶች ለመፍታት ከከተማ አሥተዳደሩና አጋር እና ባለድርሻ አካላት ጋር እየተነጋገረ ሥለመሆኑም ቡድን መሪው ተናግረዋል፡፡
አቶ አሀዱ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ከትምህርት ተቋሙ ባሻገር ወላጆች መሠረት ናቸውም ብለዋል፡፡
ወላጆች ከትምህርት ቤቶች ጋር ቅርብ ቁርኝት በመፍጠርና ለልጆቻቸው ተገቢውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ የበኩላቸውን ኀላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ መልዕክት አሥተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ሥነ-ጊዮርጊስ ከበደ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!